ሩሲያ የኮሮና ወረርሽኝን ለመግታት የጣለችውን የእንቅስቃሴ ገደብ የሚጥሱ ሰዎችን ማንነት የሚለይ ካሜራ ተከለች፡፡

258

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 26/2012 ዓ.ም (አብመድ) የኮሮና ወረርሽኝን ስርጭት ለመቆጣጠር ሞስኮን ጨምሮ ብዙ ከተሞቿ ላይ የእንቅስቃሴ ገደብ የጣለችው ሩሲያ ገደቡን ጥሰው ከቤት የሚወጡ ሰዎችን የፊት ገጽታ በትክክል መለዬት የሚችሉ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ካሜራዎችን በማቀናጀት ሥራ ላይ አውላች፡፡

የከተሞቹ ባለስልጣናት በካሜራዎቹ ተጠቅመው በየቦታው ሰዎች ከቤታቸው ሲወጡ እየተከታተሉ ቅጣት ይጥላሉ፤ ሩሲያ ግለሰቦችን በስልክ ቁጥሮቻቸው ተጠቅማ ከካሜራው ጋር በማቀናጀት የመከታተል ሐሳብም እንዳላት ተነግሯል፡፡

የኮሮና ቫይረስ የተነሳባት ቻይና ደግሞ ዛሬ በሦስት ደቂቃ ፀጥታ በኮሮና የሞቱ ዜጎቿን አስባለች፡፡ ከ3 ሺህ 300 በላይ ሰዎችን በቫይረሱ የተነጠቀችው ቻይና ዛሬ ለሦስት ደቂቃ ያክል በቆዬ ሀገር አቀፍ ፀጥታ ሟቾችን አስባለች፡፡

ሟቾች በተዘከሩበት ፀጥታ የቻይና ሰንደቅ ዝቅ ብሎ ተውለብልቧል፤ የቻይና መርከቦች፣ ባቡሮችና መኪኖች ደግሞ ለሦስት ደቂቃ የጡሩንባ ጩኸት አሰምተዋል፡፡
በቻይና ውሃን ታኅሣስ አካባቢ የተቀሰቀሰው የኮሮና ቫይረስ ከ200 በላይ ሀገራትን አዳርሷል፤ ከ180 በላይ በሆኑ ሀገራትም 60 ሺህ የሚጠጉ ሰዎችን ሕይወት ነጥቋል፡፡ በዓለም ላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርም ከ1 ሚሊዮን 118 ሺህ በላይ ሆኗል፡፡

ጣልያን 14 ሺህ 681፣ ስፔን 11 ሺህ 198፣ አሜሪካ 7 ሺህ 402፣ ፈረንሳይ 6 ሺህ 507፣ እንግሊዝ 3 ሺህ 605፣ ቻይና 3 ሺህ 326 እና ኢራን 3 ሺህ 294 ሰዎችን በቫይረሱ በማጣት ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡ በቫይረሱ በተያዙ ሰዎች ቁጥር ደግሞ 277 ሺህ 475 በማስመዝገብ አሜሪካ ቀዳሚ ሆናለች፡፡

አካላዊ ርቀትን አለመጠበቅ፣ እጆችን በየጊዜው በአግባቡ አለመታጠብ፣ ሲስሉና ሲያስነጥሱ አፍና አፍንጫን አለመሸፈን ለቫይረሱ መስፋፋት ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው፡፡

ዛሬ በአብዛኛው የኢትዮጵያ አካባቢ የገበያ ቀን ነው፤ የግድ እንድንሄድ የሚያደርገን ምክንያት ከሌላ አለመሄድ፤ ከሄድንም ርቀታችንን መጠበቅ፣ እንደ አልኮልና ሳኒታይዘር ያሉ የንጽሕና መጠበቂያዎችን ይዞ ወዲያው ወዲያው እጃችንን ማጽዳት፣ በአንገት ፎጣ፣ ኩታ ወይም በሌላ ማናቸውም ነገር አፍና አፍንጫን መሸፈን መዘንጋት የለብንም፡፡

በለቅሶ ቦታዎችም አንግት መያዝን በመተው እና ርቀትን ጠብቆ በመቆም ማስተዛዘን ቢቻል መልካም ነው፤ መልካም ቀን ያምጣልን፡፡

በአብርሃም በዕውቀት

Previous articleየጣና ሐይቅ እና የእንጅባራ ጤና ሳይንስና ቢዝነስ ኮሌጆች ለኮሮና ወረርሽኝ መከላከል ድጋፍ አደረጉ፡፡
Next articleኅብረተሰቡ ለወረርሽኙ የሚመጥን ጥንቃቄ አንዲያደርግ የምሁራን መማክርት ጉባዔው አሳሰበ፡፡