ብዝኃነታችንን የያዝንበት መንገድ…

21

ባሕር ዳር: ሐምሌ 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በርካታ ብዛኃነት ያሉባት ጥንታዊ ሀገር መኾኖን ለዓመታት በኩራት ስንናገረው ኖረናል፡፡ ታዲያ የኩራት ምንጭ የኾነውን ይህን ብዝኃነት እንዴት ነው የያዝነው?
አሁን አሁን ከሚታዩት አስፈሪ ልምዶች መካከል አንዱ የራስን በማክበር እና በማስቀጠል ሽፋን የሌላውን ማጣጣል እና ማደናቀፍ ነው፡፡

አንዳንድ ጊዜ በባሕል፣ በሃይማኖት፣ በታሪክ፣ በፖለቲካ እና በሌሎችም እሴቶቻችን ላይ ያለን አረዳድ የተለያየ ኾኖ ይገኛል። በሂደት ልዩነቱ እየሰፋ እና ችግሩን ለመፍታት የምንሄድበት መንገድ አደገኛ እየኾነም ይሄዳል፡፡ ይህ አዝማሚያ ከምናየው እና ከምንሰማው የበለጠ ችግር እንዳያመጣብን ማሰብም ይኖርብናል፡፡

ብዝኃነት እና ልዩነቶችን ተፈጥሯዊ እና ጤነኛ አድርጎ መረዳት የተሻለ አብሮነትን ይፈጥራል፡፡ የሌላውን ካልተቀበልንም ልዩነቱን ባከበረ መልኩ ሀሳባችንን ለማስረዳት እና የጋራ ሀገር ለመገንባት መፈለግ በጣም ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ከኔ የተለየ አማራጭ የተረገመ እና የተወገዘ ነው ብሎ የጠጠረ አቋም ለመተማመን ይቅርና ለመወያየት እንኳ ዕድል አይሰጥም፡፡

ታሪክ በኔ ዓይን ብቻ ይታይ ማለትም ጭራሽ ታሪክን ያጠፋው ካልኾነ በስተቀር ሊያጎላው አይችልም፡፡ የጽድቁ መንገድ የኛ ብቻ ነው ብሎ ማመኑ ባይከፋም የራስን በሌሎች ላይ ለመጫን እና የሌሎችን ለማሰናከል የሚደረግ ጥረትም ትርፉ ለራስም ሳይኾኑ መቅረት ነው፡፡

የሌላውንም እንደራስ የማየት ሥነ- ምግባር ያለው ትውልድ በሂደት ካልተገነባ በስተቀር በቤት፣ በሰፈር፣ በትምህርት ቤት፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ ተቋማት እና በሌሎችም መስኮች በጥላቻ የተቃኘ የ’እኛ እና እነሱ’ ትርክትን ይፈጠራል፡፡

ልዩነትን በመከባበር፣ በመቻቻል፣ በመወያየት እና በመግባባት መፍታት ዘላቂ ጥቅም አለው፡፡ የኔ ለሚሉት አድልቶ ሌላውን የሚመቀኝ፣ የኔ እንዲስፋፋ ሌላው ይጥፋ አይነት አስተምህሮ እና መፈክሮችም ውድቀት እንጂ ግንባታን ሲያመጡ አልታዩም፡፡

ልጆች ለጓደኞቻቸው ቀና አሳቢ፣ ሩህሩህ እና አዛኝ እንዲኾኑ፤ በጥረት እና በውጤት እንጂ ሌላውን በመመቅኘት የሕይወት መስመር እንዳይጓዙ በመቃኘት በኩል ወላጆች ሁልጊዜም ቁልፍ ሚና አላቸው ፡፡
የባሕል፣ የሃይማኖት እና የታሪክ እሴቶቻችን የምናለማበት ስልት “የራስን ጥሎ የሌላውን አንጠልጥሎ” እንዳይኾን ስጋት አለ፡፡ የኛን ለማወደስ የሌላውን ማራከስ ፋሽን እየኾነም ይስተዋላል፡፡
የሃይማኖት አስተምህሮዎቻችንን በስክነት እና በምግባር ከማስረጽ ይልቅ በጩኸት እና በጉልበት ለመጫን ስንሞክርም ይስተዋላል፡፡ በየስብከት ቦታው እና በየማኀበራዊ ሚዲያው የኔ ሃይማኖት ትክክል ነው ለማለት የሌሎችን የማጣጣል አዝማሚያዎች ተስፋፍተዋል፡፡ “የእነሱን” ሕዝብ ድጋፍ ለማግኘት “ሌላዉን” ማውገዝ የግድ የሚመስላቸው ፖለቲከኞችም ተበራክተዋል፡፡

የጋራ በኾኑ የፖለቲካ እና ምጣኔ ሃብት ጉዳዮች ላይም የሰውን ማንነት እንጂ ሃሳቡን መሞገት እየተረሳ ነው፡፡ ልዩነቶችን አክብሮ የምንጋራቸውን እሴቶች ጠብቆ ለአንድነቱም ለልማቱም የመጠቀም ዘይቤ በሚጠበቀው መንገድ እየሄደ አይመስልም፡፡

በአጠቃላይ ትውልድን ለማስቀጠል እና ሀገርን ለመገንባት በሚደረገው ሂደት ጤነኛ ያልኾኑ አስተምህሮቶች እና አዝማሚያዎች መታየታቸው የአደባባይ ምስጢር እየኾነ ነው፡፡ ቶሎ መፍትሔ ካልተበጀለትም በርካታ ብዝኃነት ያላትን ኢትዮጵያ ወደ በርካታ ደካማ መንግሥታትን እንዳይቀይራት ያሰጋል፡፡

“እኔ በግሌ፣ በቤተሰቤ፣ በአካባቢየ፣ በምሠራበት ቦታ እና አባል በኾንኩበት ተቋም ወይም በምመራው ማኀበረሰብ የራስ ወዳድነት እና ሌላውን የመጥላት ችግሮች አሉብኝ ወይ? እንዴት ልፍታ?” ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡
የጥላቻ እና የንቀት አመለካከቶችን ከራሳችን አውልቀን ስንጥል ሀገራችንን ከፉክክር ይልቅ የምክክር፣ ከመካሰስ ይልቅ የመሞጋገስ፣ ከስጋት ይልቅ የድሎት ማድረግ እንችላለን፡፡

ከራስ ወዳድነትና ሌላውን ከመጥላት ወጥተን የመተሳሰብ እና የመከባበር ሰብዕናን ስንላበስ ህጻናት እና ወጣቶችን ለአብሮነት በሚጠቅም ሰብዕና ገንብተን እናሳድጋለን፡፡ በቤት፣ በሰፈር፣ በትምህርት ቤት፣ በማኅበረሰብ አገልግሎት መስጫ እና በፖለቲካ ተቋማት ገፊ ሳይኾን አቃፊ ሥነ ምግባር የተላበሰ ትውልድ ይፈጠራል፡፡ ማኀበረሰብ ሩህሩህ፣ ይቅር ባይ እና መሃሪ እንጂ በቀለኛ እና ጨካኝ አይኾንም፡፡

በየጊዜው የምናያቸው እና የምንሰማቸው ግጭቶች፣ ወንጀሎች እና አሰቃቂ ድርጊቶች በምክንያታዊነት፣ በፍትሐዊነት እና በአርቆ አሳቢነት ያልተገነባ ትውልድ መገለጫዎች ናቸው፡፡ በሰው ሞት መደንገጣችን ቀርቶ አሰቃቂ አሟሟትንም የመላመዳችን ምክንያት የተጓዝንበት የትውልድ ሥነ ልቦና እና ሥነ ምግባር ግንባታ መንገድ የተሳሳተ መኾኑን ማሳያ ነው፡፡

የኾነው ኾኖ ቢረፍድም አልመሸም፡፡ አሁንም ራስን ቅዱስ ሌላውን ርኩስ አድርጎ ከማሰብ አስተሳሰብ ወጥተን አስፍቶ በማሰብ እና በመከባበር መኖርን እንልመድ፡፡
እንወዳታለን የምንላትን ኢትዮጵያን ለማስቀጠል የኛን ብቻ ሳይኾን የሌሎች እውነታዎችንም መቀበል ግድ ይለናል፡፡ እዚያም ቤት እሳት አለና፡፡ እየመረረንም ቢኾን የሌላውን እንደራሳችን አድርገን ማየት ሀገርን ለማስቀጠል አይነተኛ መፍትሔ ነው፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጎፋ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተፈናቀሉ ዜጎች ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ።
Next articleበደሴ ከተማ አሥተዳደር ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉት ላይ እርምጃ እየተወሰደ መኾኑ ተገለጸ።