
ባሕር ዳር: ሐምሌ 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ የተወለዱት በሰሜን ሸዋ በምንጃር ወረዳ ቀርሾ አጥር በሚባል ሥፍራ ነው።
ቤተሰባዊ ሐረጋቸው ከአጼ ምኒልክ ጋር በመተሳሰሩ አባታቸው ሲያርፉ ወደ ቤተ-መንግሥት ተወሰዱ። ከመደበኛ ትምህርታቸው ጎን ለጎንም ሙዚቃ እና ሥነ ሥዕል ይሞክሩ ነበር።
በዚህ ሁኔታ ላይ እያሉ በ1900 ዓ.ም ወደ ጀርመን ሀገር ሄደው የአውቶሞቢል አሠራር ጥበብ እንዲማሩ ዕድል ተመቻቸላቸው። በጀርመንም ከትምህርታቸው ጎን ለጎን ሹፍርና እንዲሁም የመካኒክነት ትምህርት ተከታትለው በአጥጋቢ ውጤት አጠናቀቁ።
ነጋድራስ ተሰማ አዙረው የሚያዩ ብልህ ነበሩ እና ጀርመን ሀገር ኾነው “መዲና” እና “ዘለሰኛ” ዜማዎችን እየተጫወቱ በሸክላ ተቀርጸዋል፡፡ ይህም በሸክላ የተቀረጸ የመጀመሪያው የአማርኛ ዜማ ኾኖ ተመዝግቦላቸዋል።
“ሂስ ማስተር ቮይስ” የተባለው የጀርመን የሙዚቃ
ኩባንያም ዜማዎችን በ17 ሸክላዎች ቀርጾ ስለባለቤትነት መብታቸው 17 ሺህ የጀርመን ማርክ ከፍሏቸዋል፡፡ ይህ የሙዚቃ ሥራቸውም ዛሬ ድረስ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቤተ መዘክር ውስጥ በክብር ይገኛል፡፡
ነጋድራስ ተሰማ የመጀመሪያው ሕጋዊ ባለመንጃ ፍቃድ የመኪና አሽከርካሪም ናቸው።
እኝህ ሰው ውጭ ሀገር በነበሩበት ወቅት የቅርጻ ቅርጽ ጥበብንም ተምረዋል። ወደ ሀገራቸው እንደተመለሱ የተለያዩ ዘመናዊ ቅርጻ ቅርጾችን የሠሩ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ቀራፂ ለመኾን በቅተዋል።በተጨማሪም ዘመናዊ የፎቶግራፍ አነሳስን ጥበብ ቀስመዋል። ታዲያ ጥበበኛው ሰው የጋን ውስጥ መብራት ሳይኾኑ በውጭ ሀገር የተማሩትን ሙያ በሀገር ውስጥ ወደ ተግባር ቀይረውም አሳይተዋል። ሙያቸውን ለወጣቶችም አካፍለዋል። ብዙ ተከታዮችንም እንዳፈሩ ተነግሮላቸዋል።
የታዋቂው የስፖርት ሰው የይድነቃቸው ተሰማ አባት ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ከሀገር ውስጥ አማርኛ፣ ኦሮምኛ እና አደርኛን ከውጭ ሀገራት ደግሞ ፈረንሳይኛ፣ ጣሊያንኛ፣ ጀርመንኛ እና አረብኛ ቋንቋዎችን ጥርት አድርገው ይናገሩ ነበር።
እኝህ የባለብዙ ሙያ ቀንዲል ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ በሐምሌ/1869 ዓ.ም በዚህ ሳምንት ነበር የተወለዱት።
በመረጃ ምንጭነት መዝገበ ሰብ መጽሐፍን እና ኢትዮ ዴይሊ ፖስትን ተጠቅመናል።
👉የኢትዮጵያ ወታደሮች በኮንጎ!
ኮንጎ በመካከለኛው አፍሪካ የምትገኝ በማዕድን የበለጸገች ሀገር ናት። ሀገሪቱ ለዓለም አልማዝ እና ሌሎች ማዕድናትን በማቅረብ ትታወቃለች።
የተለያዩ የከርሰ ምድር ሃብት የታደለችው ኮንጎ ከ1901 ጀምሮ በቤልጄየም ቅኝ ግዛት ሥር ስትማቅቅ ቆይታ በ1960 ነበር ነፃነቷን የተቀዳጄችው። ሀገሪቱ ነጻ ብትወጣም ቅኝ ገዥዋ ቤልጄየም አስቀድማ በጠነሰሰችው ሴራ የኮንጎ ባለሥልጣናት “በውኃ ቀጠነ” ሃሳብ ርስበርስ እንዲጋጩ አደረጋቸው።
ግጭቱ ወደ ለየለት የርስበርስ ጦርነት ተቀይሮ አያሌ የሰው ሕይዎት እና ንብረት መጥፋት ሲጀምር ተፋላሚ አንጃዎቹ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን የሰላም አስከባሪ ጓድ ተማጸኑ።
የወቅቱ የተመድ ዋና ጸሐፊ የነበሩት ስዊድናዊው ሐመር ሾልድም የሰላም አስከባሪ ጦር ሠራዊት ወደ ኮንጎ እንዲገባ የጸጥታውን ምክር ቤት አባል ሀገራትን ሠብሥበው መከሩ፤ ይሁንታም አገኙ።
ኢትዮጵያ ደግሞ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1951 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥያቄ መሠረት ጦሯን ወደ ኮሪያ አዝምታ ተልዕኮዋን በስኬት ማጠናቀቋ ይታዎሳል። በዚህ የስኬት ተሞክሮ መሠረት እ.ኤ.አ በ1960 የመንግሥታቱ ድርጅት ጦሯን ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ ወደ ኮንጎ እንድትልክ በክብር ጥያቄ ለኢትዮጵያ አቀረበላት።
የወቅቱ የኢትዮጵያ መሪም ለተመድ ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ ሰጡ። በብርጋዴር ጄኔራል ኢያሱ መንገሻ የሚመራ አንድ የክብር ዘበኛ ሻለቃ ጦርም በዚህ ሳምንት ሐምሌ 22 ቀን 1951 ወደ ኮንጎ አመራ።
የኢትዮጵያ ጦር በኮንጎ በሁለት ሥፍራዎች የግዳጅ ቀጣና ተሰጠው። የመጀመሪያው በያኔው ኦሪያንታል ጠቅላይ ግዛት በአሁኑ ኪሳንጋኒ ከተማ የሀገሪቱ መሪ በነበሩት በሉሙምባ መኖሪያ አካባቢ ሲኾን ሁለተኛው ደግሞ በቡኒያ ከተማና ዙሪያዋ ተሰማራ፡፡
ይህ በወጣት ኀይል የተገነባው አመለ ሸጋው የኢትዮጵያ ጦር በተሰማራበት ቀጣና ኹሉ ተልዕኮውን በድል ተወጣ፡፡
የጦር ሠራዊቱ አዛዥ የነበሩት ብርጋዴር ጄኔራል ኢያሱ መንገሻም ባሳዩት የመሪነት ብቃት እና ሥነ ምግባር ከተለያዩ ሀገራት ተውጣጥቶ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥላ ሥር ለተሰማራው የጦር ኀይል የኤታማዦር ኀላፊ ኾነው በመሾም የኢትዮጵያን ሥም በተመድ እና በሀገረ ኮንጎ የታሪክ ማኀደር ውስጥ በጀግንነት ማጻፍ ቻሉ።
በወቅቱ ከወታደሮች በተጨማሪም የኢትዮጵያ አውሮፕላን በተመድ ሥር ኾኖ በኮንጎ ለሰብዓዊ አገልግሎት ተግባር ተሰማርቶ ጉልህ ተግባር ማበርከቱ ይነገራል። ለኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጓድ የወቅቱ የኮንጎ መሪ
” ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ የምታኮራ ሀገር ናት፤ ሀገሪቱ እና ሕዝቧ ለዘላለም ይኑሩ! “በማለት በአደባባይ አመሥግነዋል ሲል ዩኤንቡለቲን እና አዲስ ዘመን ጋዜጣ በድረ ገጾቻቸው አስነብበዋል።
👉ዓለም ዋንጫ እና ሐምሌ!
የመጀመሪያው የዓለም የወንዶች የእግር ኳስ ዋንጫ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1930 በዑራጓይ አዘጋጅነት ተካሄዷል።
በዚህ ውድድር ላይ ከሰሜን አሜሪካ ሜክሲኮ እና አሜሪካ ተሳትፈዋል።
ከደቡብ አሜሪካ ደግሞ አርጀንቲና፣ ቦሊቪያ፣ ብራዚል፣ ቺሊ፣ ፓራጓይ፣ ፔሩ እና ዑራጓይ ተካፋይ ነበሩ።
ከአውሮፓ ቤልጄየም፣ ፈረንሳይ፣ ሮማኒያ እና ዩጎዝላቪያ ተሳትፈውበታል።
የእስያ እና የአፍሪካ ሀገራት በአንደኛው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ አልተሳተፉም።
ጨዋታዎቹ በሦስት ስታዲዬሞች 18 ግጥሚዎች ተደርገውበታል። 40 ግቦችም መረብ ላይ አርፈዋል።
ሁሉንም ጨዋታዎች 434 ሺህ 500 ሕዝብ በስታዲየሞች ተገኝቶ ተከታትሎታል።
በመጀመሪያው የዓለም የወንዶች የእግር ኳስ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ዑራጓይ አርጀንቲናን 4 ለ 2 አሸንፋ ዋንጫ በመውሰድ በታሪክ የመጀመሪያ ሀገር ኾናለች።
አሜሪካ ሦስተኛ፣ ዩጎዝላቪያ ደግሞ አራተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቅቀዋል።
አርጀንቲናዊው ጉዋሌርም ስታቢስ የተባለው ተጫዋች ስምንት ግቦችን በማስቆጠር ኮከብ ኾኖ ተሸልሟል። ታዲያ ይህ የዓለም ዋንጫ የተካሄደው በዚህ ሳምንት በ1930 ነበር በማለት ያስነበበው ኢሎ ቴሌግራፎ ነው።
👉ምሩጽ ይፍጠር ሲታዎስ!
አትሌት ምሩጽ ይፍጠር የተወለደው በትግራይ ክልል በአዲግራት ዙሪያ ነው።
ምሩጽ በ1972 በሞስኮ ኦሎምፒክ በ10 ሺህ እና በ5 ሺህ ሜትር ሩጫ ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎች ማስመዝገብ የቻለ ድንቅ አትሌት ነው።
ምሩጽ በአጨራረስ ብቃቱ በዓለም ”ማርሽ ቀያሪው” በሚል ቅጽል ስም ይታወቃል። በ1964 በሙኒክ ኦሎምፒክ በ10ሺህ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ አስመዝግቧል፡፡
አትሌቱ ከኦሎምፒክ ባለፈ በ1965 ናይጄሪያ ላይ በተካሄደው የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች በ10ሺህ ሜትር ሩጫ የወርቅ እና በ5 ሺህ ሜትር ደግሞ የብር ሜዳሊያዎች ባለቤት ኾኗል፡፡
በ1969 በተካሄደው የመላ አፍሪካ ጨዋታዎችም በ5 ሺህ እና በ10 ሺህ ሜትር ሩጫ ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎች አስገኝቷል።
በዓለም እና በአህጉር አቀፍ ውድድሮች ሰባት የወርቅ፣ አንድ የብር እና አንድ የነሐስ ሜዳሊያ በአጠቃላይ ዘጠኝ ሜዳሊያዎችን ለሀገሩ ያስመዘገበ አትሌትም ነው።
አትሌት ምሩጽ በሞስኮ ኦሎምፒክ በ10 ሺህና በ5 ሺህ ሜትር ሩጫ ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎች ማስመዝገብ የቻለው በዚህ ሳምንት በ1972 ነበር።
#ሳምንቱንበታሪክ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!