
ባሕር ዳር: ሐምሌ 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አንጋፋው ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለዓመታት በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያስተማራቸውን ተማሪዎች አስመርቋል።
ለስድስት አሥርት ዓመታት በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያስተማረው ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሀገር የምትኮራባቸውን ምሁራን አፍርቷል። ዛሬም ከዕውቀት ጅረቱ የሚያፈልቃቸውን ምሁራን ማፍራቱን ቀጥሏል።
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አካውንቲንግ እና ፋይናንስ የትምህርት ዘርፍ የዋንጫ ተሸላሚ በመኾን የተመረቀው ኤሊያስ አሸኔ በዩኒቨርሲቲው የነበረው ቆይታ ስኬታማ እንደነበር ገልጿል።
3 ነጥብ 99 በማምጣት የዋንጫ ተሸላሚ መኾኑንም ተናግሯል። ጥረት እና የፈጣሪ አጋዥነት ለስኬት እንዳበቃውም ገልጿል። በጥረቱ አስደሳች ውጤት ማስመዝገቡንም ገልጿል።
በተማረበት የትምህርት መስክ ሀገሩን ለማገልገል ቁርጠኛ መኾኑንም ነግሮናል። ሁሉም ጥረት ካደረገ ስኬታማ መኾን እንደሚችልም ነው የተናገረው።
በሳይኮሎጅ ትምህርት መስክ በማዕረግ የተመረቀችው ሕሊና ቢተው በብርታት ማጥናት፣ ጊዜን በአግባቡ መጠቀም ለስኬት እንዳበቃት ተናገራለች።
ጊዜን በአግባቡ መጠቀም ስኬታማ ውጤትን ለማምጣት ያስችላል ነው ያለችው። 3 ነጥብ 9 በማምጣት የሜዳሊያ ተሸላሚ መኾኗንም ተናግራለች።
በአስቸጋሪ የትምህርት ጊዜ ውስጥ ማለፋቸውን ያስታወሰችው ሕሊና ነገር ግን በችግር ውስጥም ኾና የሚያስደስት ውጤት ማምጣቷን ነው የተናገረችው።
መምህራን ሲያደርጉላቸው የነበረው ድጋፍ የሚደነቅ እንደነበርም አንስታለች። ተማሪዎች ለጊዜ እና ለዓላማ ልዩ ትኩረት መስጠት አለባቸውም ብላለች።
ሊገጥም የሚችለውን ችግር አስቀድሞ ማሰብ፣ ችግር ሲገጥም ደግሞ በጽናት ማለፍ ለተማሪዎች አስፈላጊ መኾኑን ተናግራለች።
በተመረቀችበት የትምህርት መስክ ሀገሯን ለማገልገል ቁርጠኛ መኾኗንም ገልጻለች። በሥነ ልቦናው ዘርፍ የራሷን አስተዋጽኦ ለማበርከት ጥረት እንደምታደርግም ተናግራለች።
በግዕዝ ቋንቋ እና ሥነ ጽሑፍ በከፍተኛ ማዕረግ ተሸላሚ በመኾን የተመረቁት መሪጌታ አብርሃም ዓለማየሁ ጊዜን በአግባቡ መጠቀም ለስኬት አብቅቶኛል ብለዋል።
ለጊዜ ልዩ ትርጉም መስጠት እና ጊዜን ከፋፍሎ መጠቀም ውጤታማ ያደርጋል ነው ያሉት። አካል ጉዳተኝነት ከስኬት እንዳላስቀራቸውም ተናግረዋል። አካል ጉዳተኞች እንችላለን የሚል መንፈስ ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል።
ይከብደኛል እና ያቅተኛል የሚል መንፈስ አላውቅም ያሉት መሪጌታ አብርሃም አካል ጉዳተኞች አስቀድመው መሸነፍ እና መፍራት የለባቸውም ብለዋል።
ሀገር በቀል ዕውቀት በኾነው የግዕዝ ቋንቋ ለሀገራቸው አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱም ገልጸዋል። መንግሥት አካል ጉዳተኞችን ሊያግዛቸው እንደሚገባም ተናግረዋል። አካል ጉዳተኞች በቴክኖሎጅ መደገፍ ይገባቸዋልም ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!