
ባሕር ዳር: ሐምሌ 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የጠዳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ያሰለጠናቸውን የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ዛሬ አስመርቋል።
በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ የጠዳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዘመነ ሀብቱ እንደ ገለጹት ዛሬ ከተመረቁት መካከል 50 በመቶ በላይ የሚኾኑት ከወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የመጡ ናቸው።
ኮሌጁ ሕዝባዊ ኀላፊነትን እየተወጣ የቆየ ተቋም ነው ያሉት የኮሌጁ ዲን በጤና ኤክስቴንሽን ሙያ ዘርፍ 80 ሴቶች ዛሬ ተመርቀዋል ብለዋል።
“ከግማሽ በላይ የሚኾኑት ተመራቂዎች ከወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የመጡ ናቸው” ያሉት የኮሌጁ ዲን የዘንድሮውን የምረቃ ሥነ ሥርዓት ለየት ያደርገዋል ብለዋል፡፡
የኮሌጁ ዲን ለእነዚህ ተማሪዎች ከክልሉ መንግሥት እና ጤና ቢሮ ጋር በመተባባር ልዩ ድጋፍ እና ክትትል የተደረገላቸው መኾኑን ተናግረዋል።
ኮሌጁ በትምህርት፣ በመማርያ ክፍሎች ግንባታ እንዲሁም በልዩ ልዩ የአሥተዳደር ዘርፎች በክልሉ ከሚገኙ ተመሳሳይ ኮሌጆች የተሻለ አፈፃፀም እያስመዘገበ በመምጣቱ በ2017 የትምህርት ዘመን በስድስት የተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በዲግሪ መርሐ ግብር ሥልጠና ይሰጣል ብለዋል።
ኮሌጁ እያከናወነ ከሚገኘው ትምህርት እና ሥልጠና ጎን ለጎንም በማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ከተለያዩ አካላት ጋር በመተባበር በ2016 ዓ.ም ከ1 ሺ 400 በላይ ለሚኾኑ የአካባቢው የኅብረተሰብ ክፍሎች የአይን ምርመራ እና ህክምና የሰጠ ሲኾን የኮሌጁን ማኅበረሰብ በማስተባበር 470 ዩኒት ደም መለገስ ተችሏል ብለዋል።
ከተመራቂዎች መካከል ከወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የመጡት ተሸላሚ ተመራቂ ሃይማኖት ነጋ እና ታድላ ወርቁ ባገኙት ዕውቀት ኅብረተሰቡን በታማኝነት እንደሚያገለግሉ ነው የገለጹት።
በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ የጎንደር ደም ባንክ ኀላፊ ደመቀ ጥላሁንን ጨምሮ የተለያዩ የተመራቂ ቤተሰቦች እና እንግዶች መገኘታቸውን ከጎንደር የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!