
ባሕር ዳር: ሐምሌ 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የከፍተኛ ትምህርት፣ የቴክኒክ እና ሙያ ሥልጠና፣ የምርምር ተቋማት እና የኢንዱስትሪ ትስስር አዋጅን ለማስጀመር እና የማስፈጸሚያ የሕግ ማዕቀፎችን ለማጽደቅ የሚያግዝ መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ የትምህርት ሚኒስትር እና የትስስር ምክር ቤቱ ሠብሣቢ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የትምህርት ተቋማት የትስስር አዋጁን በሚፈለገው ፍጥነት እና አግባብ በመተግበር ዘርፉን ውጤታማ ማድረግ እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡
በኢንዱስትሪዎች የሚደረጉ ልምምዶች ሠልጣኞች ተጨባጭ ዕውቀት እና ክህሎቶችን ይዘው እንዲወጡ ከማድረግ ባሻገር ብቁ እና ተወዳዳሪ እንዲኾኑ እንደሚያደርጋቸውም ገልጸዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር እና የትስስር ምክር ቤቱ ምክትል ሠብሣቢ መላኩ አለበል መርሐ ግብሩን በከፈቱበት ወቅት እንዳሉት የምርምር እና የትምህርት ተቋማት በትስስሩ የተፈጠረውን ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ከኢንዱስትሪ ጋር ያላቸውን ቁርኝት በማጠናከር የዘርፉ ምርት እና ምርታማነት እንዲያድግ ሊሠሩ እንድሚገባ ገልጸዋል።
ትስስሩ በተለይ ተማሪዎች በንድፈ ሃሳብ የሚያገኙትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ እና በጋራ ለመሥራት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረውም አንስተዋል።
ትምህርት፣ ሥልጠና እና ምርምርን ማበረታታት ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት የሚያስችል መኾኑን ጠቅሰው ለስኬታማነቱ የከፍተኛ ትምህርት፣ የሥልጠና እና የምርምር ተቋማትን ከኢንዱስትሪዎች ጋር ማስተሳሰር አማራጭ የሌለው ጉዳይ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ኮራ ጡሹኔ የትስስር አዋጁ ተበታትኖ የቆየውን የትምህርት ተቋማት እና የኢንዱስትሪ ግንኙነት የሚያጠናክር መኾኑን ገልጸዋል።
ከዚህ በፊት በነበረው አሠራር ተማሪዎች በኢንዱስትሪ ውስጥ የተግባር ልምምድ እንዲያደርጉ ከማድረግ አንፃር ተጠያቂነት የሰፈነበት አሠራር እንዳልነበር ጠቅሰዋል፡፡
ይህ ክፍተት በትስስር አዋጁ፣ አዋጁን መሠረት በማድረግ በተዘጋጁ እና በቀጣይ በሚጸድቁ የሕግ ማዕቀፎች የነበረውን ክፍተት የሚሞላ መኾኑን መናገራቸውን ከትምህርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!