
ባሕር ዳር: ሐምሌ 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ገበያን ለማረጋጋት የሚያግዙ የፍጆታ ምርቶችን ቀጥታ ከአርሶ አደሩ እና ከውጪ ገዝቶ እያቀረበ መኾኑን ገልጿል።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አሥፈፃሚ አቻ ደምሴ ኮርፖሬሽኑ ገበያን ለማረጋጋት የሚያግዙ የፍጆታ ምርቶችን ቀጥታ ከአርሶ አደሩ እና ከውጪ ገዝቶ እያቀረበ ነው ብለዋል።
ከሀገር ውስጥ ገበያ ላይ የጤፍ፣ የስንዴ፣ የበቆሎ፣ የዳቦ ዱቄት እና ሌሎች የግብርና ምርቶች ተገዝተው በኮርፖሬሽኑ የግብይት ማዕከላት በኩል ለኅብረተሰቡ እየቀረቡ መኾኑን ተናግረዋል።
ከሀገር ውጪም የምግብ ዘይት በስፋት እየተገዛ መኾኑን ገልጸው ይህም ያለውን የገበያ ክፍተት ለመሙላት የሚያግዝ መኾኑን ነው የተናገሩት።
የኮርፖሬሽኑ የቡና እና እህል ግብይት ምክትል ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ገመቺስ መላኩ ከአንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ጤፍ፣ ስንዴ፣ በቆሎ፣ የዳቦ ዱቄት፣ ስኳር እና ሌሎች ምርቶች ተገዝተው በኮርፖሬሽኑ የግብይት ማዕከላት በኩል ቀርበዋል ብለዋል።
የአትክልት እና ፍራፍሬ ምርቶች በስፋት ተገዝቶ እየቀረበ መኾኑን የገለጹት ምክትል ዋና ሥራ አሥፈፃሚው የገበያ የአቅርቦት ጉድለት በሚኖርባቸው ቦታዎች ላይ ጭምር ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
እንደ ኢዜአ ዘገባ ኮርፖሬሽኑ በቂ የፍጆታ ምርቶች ክምችት በየማዕከላቱ እንዳለው አረጋግጠዋል። ኮርፖሬሽኑ በተለያዩ ክልሎች 28 የግብይት ማዕከላት ያሉት ሲኾን ከየክልሎቹ ንግድ ተቋማት ጋር በቅርበት እየሠራ መኾኑም ተገልጿል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!