የመካከለኛ ርቀት ውድድሮች ዛሬ ይካሄዳሉ፡፡

51

ባሕር ዳር: ሐምሌ 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በ33ኛው የፓሪስ ኦሎምፒክ የኢትዮጵያ አትሌቶች የሚወዳደሩባቸው የመካከለኛ ርቀቶች ዛሬ ይካሄዳሉ፡፡

በ800 ሜትር ርቀት በሴቶች የሁለተኛ ዙር ማጣሪያ ዛሬ ከቀኑ 6፡20 ላይ ይካሄዳል፡፡ በዚህ ውድድር አትሌት ሀብታም ዓለሙ የሁለተኛ ዙር የግማሽ ፍጻሜውን ለማለፍ ትወዳደራለች።

አትሌት ሀብታም በመጀመሪያው ዙር ማጣሪያ ርቀቱን 2 ደቂቃ ከ2 ሴኮንድ ከ19 ማይክሮ ሴኮንድ በመሮጥ ሰባተኛ መውጣቷ ይታወቃል።

ይህ የሁለተኛው ዙር የማጣሪያ ውድድር በአራት ምድብ ተከፍሎ የሚካሄድ ሲኾን ከየምድቡ አንደኛ የሚወጡ አትሌቶች በቀጥታ ወደ ግማሽ ፍጻሜው የሚያልፉ ይኾናሉ፡፡ ከቀጥታ አላፊዎቹ በተጨማሪም ሁለት ፈጣን ሰዓት ያላቸው ተወዳዳሪዎች ግማሽ ፍጻሜውን ይቀላቀላሉ።

የ1ሺህ 500 ሜትር የወንዶች ሁለተኛ ዙር የማጣሪያ ውድድርም ዛሬ ምሽት 2፡15 ላይ ይካሄል፡፡ በርቀቱም አትሌት አብዲሳ ፈይሳ ተሳታፊ ይኾናል፡፡

አትሌቱ አብዲሳ በመጀመሪያው ማጣሪያ ርቀቱን በ3 ደቂቃ ከ39 ሴኮንድ ከ67 ማይክሮ ሴኮንድ በመሮጥ 14ኛ መውጣቱ ይታወሳል፡፡ የዛሬው ውድድርም ወደ ግማሽ ፍጻሜው ለማለፍ የሚያደርገው ሁለተኛ ዕድሉ ይኾናል፡፡

የዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በ33ኛው ኦሎምፒክ ጨዋታዎች መሰናክልን ጨምሮ ከ200 እስከ 1ሺህ 500 ሜትር ርቀቶች ሁለተኛ ዕድል የተሰኘ አዲስ አሠራር መጀመሩን ግልጽ አድርጓል፡፡

በአዲሱ የውድድር መመሪያ መሠረት መሰናክልን ጨምሮ ከ200 እስከ 1ሺህ 500 ሜትር ርቀቶች የሚሳተፉ አትሌቶች በመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ ቀጥታ ወደ ቀጣዩ ዙር ባያልፉም በድጋሚ ወደ ግማሽ ፍጻሜ መግባት በሚያስችላቸው የሁለተኛ ዙር ማጣሪያ ውድድር የመካተት ዕድል እንደሚያገኙ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ25 ሺህ በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን የምዕራብ ጎንደር ዞን ሥራ እና ሥልጠና መምሪያ አስታወቀ።
Next article“ገበያን ለማረጋጋት የሚያግዙ የፍጆታ ምርቶችን ቀጥታ ከአርሶ አደሩ እና ከውጪ ገዝቸ እያቀረብኩ ነው” የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን