
ገንዳ ውኃ: ሐምሌ 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ዮሐንስ ከተማ አሥተዳደር በማኅበር ተደራጅተው የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ወጣቶች መካከል በዕውቀት አስማማው እና ጓደኞቹ የቤት እና የቢሮ ዕቃዎች ማምረቻ እና መሸጫ የኅብረት ማኅበር አንዱ ነው።
ከተማ አሥተዳደሩ ባመቻቸላቸው የመሥሪያ ቦታ እና የብድር አገልግሎት ወደ ሥራ መግባታቸውን የማኅበሩ ሠብሣቢ ወጣት በዕውቀት እዘዘው ነግረውናል።
በከተማዋ በኢንተርፕራይዝ ከተደራጁ ማኅበራት መካከል ዋሲሁን፣ እሱባለው እና ጎደኞቹ የእንግዳ ተቀባይ ኅብረት ሽርክና ማኅበር አንዱ ነው።
ከ80 በላይ አባላት ያለው ይህ ማኅበር በህልውና ዘመቻ የተሳተፉ ወገኖችን ጨምሮ ሌሎች ሥራ አጥ ወጣቶችን በማካተት ወደ ሥራ መግባቱን የማኅበሩ ሠብሣቢ ወጣት ሙሉቀን ገብረሥላሴ ተናግረዋል።
በተፈጠረላቸው የሥራ ዕድል የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መኾናቸውንም ወጣቶቹ አንስተዋል።
በመተማ ዮሐንስ ከተማ አሥተዳደር በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ከ400 በላይ ማኅበራትን በማደራጀት ከ1 ሺህ 300 በላይ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩን የከተማ አሥተዳደሩ ሥራ እና ሥልጠና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ድንቃየሁ ተስፋዬ ተናግረዋል።
እንደ አቶ ድንቃየሁ ገለጻ የሥራ ዕድል ለተፈጠረላቸው ወጣቶች የመሥሪያ እና የመሸጫ ቦታ በማመቻቸት ወደ ሥራ ተገብቷል።
ከፋይናንስ አበዳሪ ተቋማት ጋር በመተባበር ለወጣቶች የብድር አገልግሎት በማመቻቸትም የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ታልሞ መሠራቱንም አንስተዋል።
በህልውና ዘመቻው መስዋዕትነት የከፈሉ ወገኖችን የቅድሚያ ቅድሚያ የሥራ ዕድል በመፍጠር ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በትኩረት ሢሠራ መቆየቱንም አቶ ድንቃየሁ ጠቁመዋል።
በተጠናቀቀው 2016 በጀት ዓመት በዞኑ ከ26 ሺህ 800 በላይ ዜጎች በቋሚ እና በጊዜያዊነት የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ እስካሁን ከ25 ሺህ 800 በላይ ዜጎች በተለያዩ ዘርፎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን የዞኑ ሥራና ሥልጠና መምሪያ ምክትል ኀላፊ አስፋው በሪሁን ተናግረዋል።
ከእነዚህ መካከል 17 ሺህ የሚጠጋው በቋሚ ሲኾን 8 ሺህ የሚኾነው ደግሞ በጊዜያዊ የሥራ ዕድል የተፈጠረለት ነው ብለዋል፡፡
በዚህም የዕቅዱን 91 በመቶ መፈጸም መቻሉን ነው አቶ አስፋው ያነሱት። የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው መካከል ከ17 ሺህ 800 በላይ ወንዶች ሲኾኑ 8 ሺህ የሚጠጉት ደግሞ ሴቶች ናቸው ብለዋል።
የሥራ ዕድል ለተፈጠረላቸው ወጣቶችም በገጠር እና በከተማ ግብርና፣ በማዕድን፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኮንስትራክሽን፣ በንግድ እና በሌሎች ዘርፎች ከ24 ሺህ በላይ ጸጋዎችን በመለየት ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
የወጣቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲሁም በወጣቶች የሚነሱ የመስሪያ ቦታ እና የብድር አገልግሎት ጥያቄዎችን ለመፍታት የሚችል ግብረኀይል ተቋቁሞ ሢሠራ መቆየቱንም ነው አቶ አስፋው ያነሱት።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የሥራ ዕድል ለተፈጠረላቸው ዜጎች ከ57 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰራጭቷል ያሉት ምክትል ኀላፊው ከዚህ ውስጥም 34 ሚሊዮን የሚኾነው ከባለፈው ዓመት ተዘዋዋሪ ብድር የተመለሰ እንደኾነ ገልጸዋል።
በማኅበር ለተደራጁ ወጣቶች ከ160 ሚሊዮን ብር በላይ የገበያ ትሥሥር ለመፍጠር ታቅዶ እሰከ በጀት ዓመቱ ማጠናቀቂያ ከ120 ሚሊዮን ብር በላይ የገበያ ትሥሥር መፍጠር መቻሉንም አንስተዋል።
ለወጣቶቹ 163 ሺህ ካሬ ሜትር የመሥሪያ ቦታ ከማመቻቸት ባለፈ ከመንግሥት እና ከማኅበረሰቡ በተሠበሠበ 4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የመሥሪያ ሸድ መገንባቱም ተጠቁሟል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!