
ባሕር ዳር: ሐምሌ 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያስተማራቸውን ተማሪዎች አስመርቋል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሥራ አመራር ቦርድ አባል አስቴር ዘውዴ መማር መመራመር፣ ዕውቀትን እና ጥበብን መሻት ሀገር ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ ምክንያት የኾነ ታላቅ ኀይል ነው ብለዋል።
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ላሳለፈው ስኬታማ ዓመታት በኢትዮጵያ ከሚጠቀሱ የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች መካከል በግንባር ቀደምትነት እንደሚጠራም ተናግረዋል።
እጅግ በፈጣን ዕድገት የሚገኝ ዩኒቨርሲቲም ነው ብለዋል። ለዚህ ስኬት ላበቁት ሁሉ ምሥጋና ይገባቸዋል ነው ያሉት።
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሀገር ኩራት ነው ብለዋል። “ከዓባይ ጓዳ ጥበብ ሲቀዳ” በሚል መርሁ በዓለም ዙሪያ ለሚታወቀው የዩኒቨርሲቲው ስኬታማነት በአንድነት እና በጥምረት መሥራት ይገባል ነው ያሉት።
“ተመራቂዎች ለዓመታት የደከማችሁበትን ውጤት ለምታዩባት ቀን በመድረሳችሁ እንኳን ደሰ አላችሁ” ብለዋል። ትምህርት እና መመራመር መቼም አያልቅም ያሉት ወይዘሮ አስቴር በሥራ ዓለም የተማሩትን የበለጠ እንዲያጎለብቱ አሳስበዋል።
በሥራ ዘመናቸው ማንነታቸውን ሙሉ የሚያደርጉበት፣ ሀገራቸውን የሚያገለግሉበት ዕድል ያገኙበት መኾኑንም ተናግረዋል። ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ ብሎም ለመምህራን እና ወላጆቻቸው ዋጋ እንዲሰጡም አደራ ብለዋል።
ኢትዮጵያ ችግሮቿን በምርምር የሚፈቱ ትውልዶችን እንደምትፈልግም ተናግረዋል። በሀገር ፍቅር ስሜት፣ በታማኝነት እና በቁርጠኝነት ኀላፊነታቸውን እንደሚወጡም ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!