“የተማሪዎች ስኬት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስኬት ማሳያ ነው” መንገሻ አየነ (ዶ.ር)

91

ባሕር ዳር: ሐምሌ 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያስተማራቸውን ተማሪዎች አሥመርቋል። አንጋፋው ዩኒቨርሲቲ 8 ሺህ 524 ተማሪዎችን እያስመረቀ ነው።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ መልዕክት ያስተላለፉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት መንገሻ አየነ (ዶ.ር) ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ባለፉት ሥድስት አሥርት ዓመታት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ምሁራንን ለሀገር እና ለዓለም አቀፍ አበርክቷል ብለዋል።

ዛሬ የተመረቁ ተማሪዎችም ችግር ፈቺ እና አስታራቂ ለመኾን ከቀድሞዎቹ ጎራ በመሰለፋቸው እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋቸዋል።

ብዙ ችግር አልፈው እዚህ በመድረሳቸውም ኩራት እንደሚሰማቸው ነው የተናገሩት። የተማሪዎች ስኬት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስኬት ማሳያ መኾኑንም ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው እንደ ሀገር ለተያዙ የራስ ገዝነት እና የምርምር ዘርፎች በትኩረት እየሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል። ችግር ፈቺ ምርምሮችን በማቅረብ፣ ለማኅበረሰብ እና ለሀገር የሚጠቅሙ የምርምር ውጤቶችን በማሳየት፣ ዓለም አቀፋዊነትን ታሳቢ ያደረጉ በርካታ ሥራዎችን እየሠራም ነው ብለዋል።
ለሀገር በቀል ዕውቀቶች ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። ሥራዎቻቸው ማኅበረሰቡን መሠረት ያደረጉ መኾናቸውንም አስታውቀዋል።

ፈር ቀዳጅ የኾኑ የማሪታይም ተማሪዎችን እያስተማረ መኾኑንም ገልጸዋል። ዩኒቨርሲቲው ዓለም አቀፋዊነትን ከጊዜ ወደጊዜ እያጎላ የመጣ መኾኑንም ተናግረዋል። ከአፍሪካ ምርጥ 100 ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንደኛው መኾኑንም አንስተዋል። ዩኒቨርሲቲው የውጭ ሀገራት ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ መኾኑንም ተናግረዋል። ከሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር እየሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል። በጥራት እና ተቋማዊ ጥንካሬ ተጠቃሽ መኾኑንም አንስተዋል።

ፕሬዚዳንቱ ሀገራዊ እና አካባቢያዊ ፋይዳ ያላቸውን ሥራዎች እየሠራ ነው ብለዋል። እንደ ሀገር ችግሮች ቢገጥሙም ዩኒቨርሲቲው እሴቶችን በማስጠበቅ እየቀጠለ መኾኑንም ተናግረዋል። ዩኒቨርሲቲው ብቁ እና ታታሪ ተማሪዎችን በማፍራት እንደሚታወቅም አስታውቀዋል።

ዩኒቨርሲቲው የመውጫ ፈተና ከሰጣቸው ተማሪዎች በአማካይ ከፍተኛ ውጤት አስመዝግበው ማለፋቸውንም ተናግረዋል። የመውጫ ፈተና ከሰጡባቸው 78 የትምህርት ክፍሎች መካከል 38 የትምህርት ክፍሎች ሁሉንም ተማሪዎቻቸውን አሳልፈዋል። 16 ደግሞ በእያንዳንዳቸው አንድ ተማሪ ብቻ ሲቀር ሁሉንም አሳልፈዋል ነው ያሉት። ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምሳሌ የሚኾን መኾኑንም አንስተዋል። በሀገር በቀል ዕውቀት የሚሠሩትን ሥራ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል። ባሕር ዳር ከተማ የትምህርት፣ የሳይንስ እና የምርምር ከተማ ኾና እንድትቀጥል ዩኒቨርሲቲው የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላልም ነው ያሉት። ኢትዮጵያ ብዙ ያልተነካ ሃብት እና ዕድል አላት ያሉት ፕሬዚዳንቱ ያላትን ዕድል እና ሃብት ለመጠቀም አዲስ ትውልድ እና ኀይል ያስፈልጋታል ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው ኢትዮጵያ የምትፈልገውን ለማበርከት በስፋት እና በጥራት እያሰለጠነ መኾኑንም ተናግረዋል። ተመራቂዎች መሪ፣ ተመራማሪ፣ አዲስ ነገር ፈጣሪ እና ችግር ፈቺ እንዲኾኑም አሳስበዋል። ተመራቂዎች በዓላማ ጸንተው እና በሙያ ሥነ ምግባር ተቃኝተው ሀገራቸውን እንዲያገለግሉም አደራ ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹን እያስመረቀ ነው።
Next article“ኢትዮጵያ ሀገር ወዳድ እና ታታሪ ትውልድ የምትፈልግበት ወቅት ነው” የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሥራ አመራር ቦርድ አባል አስቴር ዘውዴ