“በሀገር ላይ ጉዳት ሊያደርሱ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ በመሥራት ውጤት ተመዝግቧል” የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት

18

ባሕር ዳር: ሐምሌ 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት በሰጠው መግለጫ እንዳለው በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ከማቅረብ እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ ከመርዳት ወንጀሎች ጋር በተያያዘ የተሰጠውን ሀገራዊ ተልዕኮ መሠረት በማድረግ በ2016 በጀት ዓመት በሀገር ኢኮኖሚ እና ደኅንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ወንጀሎችን በመለየት ውጤታማ ተግባራትን አከናውኗል።

በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመደገፍ ወንጀሎች በሀገር ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ሕይዎት ላይ የሚያደርሱት ጉዳት ከፍተኛ ነው፡፡ በመኾኑም በሀገሪቱ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ሚና ለይቶ በዝርዝር ያስቀመጠ የሕግ ማዕቀፍ ወጥቶ ተግባራዊ በመደረግ ላይ ነው።

በዚሁ መሠረት አገልግሎቱ በ2016 በጀት ዓመት ወደ 4 ሺህ የሚጠጋ የአጠራጣሪ ግብይት መረጃዎች ከሪፖርት አቅራቢ ተቋማት ደርሰውታል። ከተለያዩ ጠቋሚዎች 200 የሚኾኑ ወንጀል ነክ ጥቆማዎችን ተቀብሏል። በክትትል እና ፍተሻ በርካታ ተጨማሪ ወንጀል ነክ መረጃዎችን በመሠብሠብ ለራሱ እንዲሁም ለባለድርሻ አካላት በማስተላለፍ ለወንጀል መከላከል እና መቆጣጠር ሥራ እንዲውሉ አድርጓል።

አገልግሎቱ በበጀት ዓመቱ እነዚህን ወንጀል ነክ ጉዳዮች መሠረት በማድረግ ባካሄደው ዝርዝር ፍተሻ እና የማጥራት ሥራ ቅድሚያ የሚሰጣቸው 310 ከልዩ ልዩ ወንጀሎች ጋር ግንኙነት ያላቸው ወንጀል ነክ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ትንተና በማድረግ የሕግ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ለሚመለከታቸው አካላት ተላልፎ በሂደት ላይ ይገኛል።

ከእነዚህ ጉዳዮች መካከል ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ የማጭበርበር ወንጀል፣ የታክስ፣ የኮንትሮባንድ ንግድ፣ የሙስና፣ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ማስገደድ እና ማስፈራራት፣ ሃብት ማሸሽ፣ ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍ እና ከሌሎች ወንጀሎች ጋር ግንኙነት ያላቸው ናቸው።

እነዚህ የወንጀል ድርጊቶች በቢሊዮን ብር የሚቆጠር በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የነበሩ እና ያደረሱ መኾናቸው ተለይቷል። በወንጀል ድርጊቱም በተለያየ ደረጃ ተሳትፎ እንዳላቸው የተጠረጠሩ 2 ሺህ 273 ግለሰቦች እና ሌሎች አካላት ተለይተው በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ ጉዳዮቹ በሕግ ተይዘው በሂደት ላይ ይገኛል።

የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀሎችን ከመከላከል እና ከመቆጣጠር ጋር በተያያዘ ወንጀሎቹን የመከላከል ኀላፊነት ያለባቸው የፋይናንስ ተቋማት እንዲሁም ፋይናንስ ነክ ያልኾኑ የንግድ እና ሙያ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ አካላት በሕግ የተጣለባቸውን ግዴታዎቻቸውን መወጣት እንዲችሉ የክትትል እና ቁጥጥር ሥራዎችን የሚያከናውን ሲኾን በያዝነው በጀት ዓመትም ይህ ተግባር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ተጠናከሮ እንደሚቀጥልም ተገልጿል።

ከእነዚህ ወንጀሎች ጋር በተያያዘ አገልግሎቱ በራሱ መረጃ ምንጮች እና ከባለድርሻ አካላት በሚደርሱ ጥቆማዎች አጠራጣሪ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ ወንጀሎቹ እንዳይፈጸሙ የመከላከል እርምጃዎችን ሲወስድ ቆይቷል።

ወንጀሎቹ በድብቅ እና ሕጋዊ በሚመስል አግባብ በሽፋን የሚፈጸሙ በመኾናቸው የመከላከል እና መቆጣጠር ሥራውም ተመጣጣኝ የባለድርሻ አካላት ትብብር እና ቅንጅት ይጠይቃል። በዚህ ረገድ በሀገር አቀፍ ደረጃ ወንጀሎቹን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ተቋቁሞ በሥራ ላይ የሚገኘው ብሔራዊ ኮሚቴ ለሀገራዊ ትብብር እና ቅንጅት የፈጠረውን ተጨማሪ ዕድል እንዲሁም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ያለንን የግንኙነት ሥርዓት በማጠናከር የፋይናንስ ሥርዓቱ ለወንጀል የማይመች እንዲኾን የጀመራቸውን እርምጃዎች አጠናክሮ ይቀጥላል።

ተቋሙ የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት እነዚህ ወንጀሎች በሀገር ላይ የሚያደርሱትን ከፍተኛ ጉዳት መሠረት በማድረግ ለመከላከል እና መቆጣጠር ሥራው የሚጠበቅበትን ኀላፊነት በላቀ ደረጃ ለመወጣት በትኩረት እንደሚሠራ በዚሁ አጋጣሚ እየገለጸ ኅብረተሰቡም ጥቆማ በመስጠት እያደረገ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አስተላልፏል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለኤች አይ ቪ ኤድስ ከዚህ በፊት የሰጠነውን ትኩረት በመድገም አዲሱን ትውልድ ከበሽታው መታደግ እንደሚገባ ተገለጸ።
Next articleአምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ በሱዳን የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛን ተቀብለው አነጋገሩ።