
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 26/2012 ዓ.ም (አብመድ) የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማ (ኢንጂነር) ዛሬ በኮሮና ወረርሽኝ መከላከል ዙሪያ እየተሠሩ ያሉ ጉዳዮችን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ ምክትል ከንቲባው እንዳስታወቁት በመዲናዋ ስለወረርሽኙ ግንዛቤ ለመፍጠር፣ ድጋፍ ለማሰባሰብና ሌሎችም ተግባራትን ለመከወን ከ30 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ተሰማርተዋል፡፡
ከግለሰቦችና ከልዩ ልዩ ድርጅቶችና ተቋማት በዓይነትና በጥሬ ገንዘብ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መሰብሰቡንም ኢንጂነር ታከለ ዑማ ገልጸዋል፡፡
ለለይቶ ሕክምና ክትትል ማድረጊያ እንዲውሉ 40 ሆቴሎችና 30 የመኖሪያ ቤቶች በስጦታ መበርከታቸውንም አስታውቀዋል፡፡
የከተማዋ ነዋሪዎችን የኢኮኖሚ ችግር ለማቃለል በሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት አማካኝነት የፍጆታ ሸቀጦችን በበቂ መጠን ለማቅብ እየተሠራ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ ምክትል ከንቲባው እንዳስታወቁት በሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል ከአትክልት እስከ ጤፍና የምግብ ሸቀጦች ለማቅረብ በቂ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል፡፡
ከገበያ ማረጋጋት ጎን ለጎን ሕገ ወጥ ትርፍ ለማግኘት ገበያ በሚያስርቡና ያላግባብ ዋጋ በሚጨምሩ ነጋዴዎች ላይ እየተወሰደ ያለው ሕግን የማስከበር ርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመላክተዋል፡፡
አካላዊ ቅርርብን ለማስቀረት የተቀራረቡ የገበያ ማዕከላትን ወደ ሰፊ አካባቢዎች በጊዜያዊነት ማዛወር መጀመሩንም አስታውቀዋል፤ ታዋቂውን የአትክልት ተራ ገበያ ወደ ጃንሜዳ በጊዜያዊነት መዛወርም በአብነት አንስተዋል፡፡
በአዲስ አበባ የተከሰተውን የንጹሕ መጠጥ ውኃ እጥረት ለመቅረፍ እየተሠራ መሆኑን ያመለከቱት ኢንጂነር ታከለ ዑማ በጊዜያዊ መፍትሔነት ወደ 35 የውኃ ቦቴዎችን ተጠቅሞ ውኃ እየቀረበ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ሰጠኝ እንግዳው -ከአዲስ አበባ
ፎቶ፡- ከአዲስ አበባ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ገጽ