
ባሕር ዳር: ሐምሌ 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል የኤች አይ ቪ ኤድስ የሥርጭት መጠን በጥቅል ሲታይ 1 ነጥብ 2 በመቶ እንደኾነ በክልሉ የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከል እና መቆጣጠር ዘርፈ ብዙ ምላሽ ዳይሬክተር ውድነህ ገረመ ተናግረዋል፡፡ በክልሉ ሥርጭቱ በወረርሽኝ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲኾን በአብዛኛው በከተሞች ላይ በስፋት እንደተስፋፋ ነው የገለጹት፡፡
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ጥናት እንደሚያሳየው ከ30 እስከ 44 የዕድሜ ክልል ባለው የኀብተሰብ ክፍል የሥርጭት መጠኑ እንደሚጨምር አቶ ውድነህ ተናግረዋል፡፡ በዚህ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ተጋላጭ የኾኑ የማኀበረሰብ ክፍሎች እንደኾኑ ነው የተናገሩት፡፡ በማኀበረሰቡ በኩል የኤች አይ ቪ ኤድስን ምንነት በደንብ የመረዳት፣ የመተላለፊያ መንገዶችን በትክክል የማወቅ እና መከላከያ ዘዴዎችንም ጠንቅቆ የመጠቀም እና በተግባር የማዋል ዝንባሌ ዝቅተኛ እንደኾነ ይገልጻሉ አቶ ውድነህ፡፡
አቶ ውድነህ አክለውም ከአሁን በፊት በነበሩ ዓመታት በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች በዓለም አቀፍ ደረጃ በጀት ተመድቦለት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ወረርሽኙን ለመግታት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በየደረጃው በመረባረብ ሰፊ ሥራዎች ይሠራ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ በአምስት ዓመቱ በጥቅል ያለው ሥርጭት ሲታይ በፊት ከነበረው አሁን የቀነሰ እንደኾነ ጥናቶች ያሳያሉ። ከዚህ ጋር ተያይዞ በአዲስ የመያዝ መጠን 90 በመቶ፣ ከኤች አይ ቪ ጋር ተያይዞ የሚከሰት ሞት 70 በመቶ የቀነሰ እንደኾነም ነው አቶ ውድነህ የተናገሩት፡፡
አያይዘውም ቫይረሱ ያለበት ሰው ተመርምሮ ሕክምናውን ተከታትሎ የቫይረስ መጠኑን ዝቅተኛ ደረጃ ወይም በምርመራ በማይለይበት ደረጃ ላይ በማድረስ በአዲስ የማሠራጨት መጠኑን መቀነስ ይኖርበታል ብለዋል አቶ ውድነህ፡፡ በሽታው በከፍተኛ ሁኔታ በተስፋፋበት ወቅት ከወላጆቻቸው ቫይረሱ የተላለፈባቸዉ ህጻናት አሁን የወጣትነት ዕድሜ ላይ ደርሰዋል፡፡
አቶ ውድነህ የበሽታውን ሥርጭት የመከላከል እና የመቆጣጠር ተግባር እየተከናወነ እንደኾነም አስርድተዋል። ወጣቶችን በማኀበር በማደራጀት፣ የሕይዎት ክህሎት ሥልጠና በመስጠት ሕይዎታቸውን በአግባቡ እንዲመሩ ሥራዎች እየተሠሩ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ሴቶች ላይ ተዘዋዋሪ ብድር በግሎባል ፈንድ ተሰጥቶ 52 ከተሞች ላይ ሥራ በመሥራት ወደ 12 ሺህ የሚኾኑ ሴቶች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲኾኑ ተደርጓል፡፡ በሁሉም ዞን እና ወረዳዎች 10 ተጋላጭ የኾኑ የኀብረተሰብ ክፍሎችን በመለየት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ በሰፊዉ እየተሠራ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡
አቶ ውድነህ የሚሠራው ሥራ ከበሽታው ሥርጭት አኳያ ሲታይ በቂ እንዳልኾነ ይናገራሉ፡፡ በአጠቃላይ ኤች አይ ቪ ኤድስን ሥራ አንድ ተቋም ብቻ የሚሠራው አይደለም ይላሉ አቶ ውድነህ። በሽታውን በመከላከል እና በመቆጣጠር ረገድ የሁሉንም ሴክተሮች እና የሁሉንም የኀብረተሰብ ክፍሎች ርብርብ ይጠይቃል ያሉት አቶ ውድነህ ከዚህ በፊት የሰጠነውን ትኩርት በመድገም አዲሱን ትውልድ መታደግ ይገባዋል ብለዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!