በምዕራብ ጎንደር ዞን እስካሁን ከ140 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በአኩሪ አተር ሰብል መልማቱን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

15

ገንዳ ውኃ: ሐምሌ 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን በ2016 /2017 የመኾር የእርሻ ወቅት ከ518 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለማልማት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን የዞኑ ግብርና መምሪያው ምክትል ኀላፊ ጤናው ፈንታሁን ተናግረዋል። በበጀት ዓመቱ በዞኑ ለውጭ ምንዛሬ ዕድገት እና ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውሉ እንደ ሰሊጥ፣ ጥጥ እና አኩሪ አተር ሰብሎች በስፋት እየለሙ መኾኑንም አቶ ጤናው አንስተዋል።

ምክትል መምሪያ ኀላፊው እንደገለጹት በዞኑ ከ176 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በአኩሪ አተር ሰብል ለመሸፈን የታቀደ ሲኾን እሰካሁን ከ140 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ማልማት ተችሏል፡፡ ከዚህ ውስጥ 95 ሺህ ሄክታር የሚኾነው በኩታ ገጠም የለማ ሲኾን በሄክታር ከ28 እስከ 30 ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ ነው ብለዋል።

ከሚለማው የአኩሪ አተር ሰብል 5 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ ምርት የሚጠበቅ ሲኾን ምርቱ ለኢንዱስትሪ ግብዓት ብቻ የሚውል ይኾናል። ምርታማነትን ከባለፈው ዓመት በተሻለ ለማሳደግም ከምርጥ ዘር እና ከአፈር ማዳበሪያ ግብዓት አቅርቦት በተጨማሪ አልሚዎች በሜካናይዜሽን እና በኩታ ገጠም እንዲያለሙ በትኩረት እየተሠራ ስለመኾኑም አቶ ጤናው አንስተዋል።

በመተማ ወረዳ የኮኪት ቀበሌ ነዋሪ የኾኑት አቶ ሰይድ አሊ ካላቸው 40 ሄክታር መሬት 10 ሄክታር የሚኾነውን በአኩሪ አተር ሰብል መሸፈናቸውን ተናግረዋል። ከዚህም በሄክታር ከ20 እስከ 25 ኩንታል ምርት ለማግኘት ተግተው እየሠሩ መኾኑን ነው የገለጹት። ሌላው በመተማ ወረዳ የደለሎ ቀበሌ ነዋሪ የኾኑት አቶ አስረስ ደምለው 25 ሄክታር መሬት በአኩሪ አተር ሰብል መሸፈናቸውን ተናግረዋል። እያለሙት ካለው ሰብል ከ4 መቶ ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት አቅደው እየሠሩ መኾኑን ነው የተናገሩት።

የሚጠብቁትን ምርት ለማግኘት እና ከባለፈው ዓመት በተሻለ መልኩ ለማሳደግ የማንጣፈፍ ሥራ እና በቂ የአፈር ማዳበሪያ መጠቀማቸውን ተናግረዋል። በ2016/2017 የምርት ዘመን ለማልማት ከታቀደው 518 ሺህ 700 ሄክታር መሬት ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ከ507 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች መሸፈኑ ተጠቁሟል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የ2017 በጀት ዓመት ያለፈው ችግር ጥላውን እንዳያጠላበት የምናደርግበት ዓመት ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next articleለኤች አይ ቪ ኤድስ ከዚህ በፊት የሰጠነውን ትኩረት በመድገም አዲሱን ትውልድ ከበሽታው መታደግ እንደሚገባ ተገለጸ።