
ባሕር ዳር: ሐምሌ 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል ከፍተኛ እና መካከለኛ መሪዎች የ2016 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ መድረክ እየተካሄደ ነው። በመድረኩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ አፈጉ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬን ጨምሮ ከፍተኛ መሪዎች ተገኝተዋል።
በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በ2016 በጀት ዓመት በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ዕቅዱን በተገቢው መንገድ መፈጸም አልተቻለም ነው ያሉት። “አብዛኛውን ጊዜ ያሳለፍነው የክልሉን ሰላም እና ጸጥታ በማረጋጋት፣ ለልማት እና መልካም አሥተዳደር ምቹ በማድረግ ነው” ብለዋል።
ከጸጥታ ሥራው ጎን ለጎን የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች መሥራታቸውንም አመላክተዋል። በተለይም አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች በርካታ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች መሠራታቸውን ነው የተናገሩት። የ2017 በጀት ዓመት ያለፈው ዓመት እና ከዚያ በፊት በነበሩ ጊዜያት ያልተፈጸሙ ሥራዎች ጭምር የሚሠሩበት ነው ብለዋል። የ2017 በጀት ዓመት ያለፉት የስትራቴጂክ ዕቅድ ዓመታት ማጠናቀቂያ መኾኑንም አንስተዋል።
በበጀት ዓመቱ ከታቀዱ ሥራዎች ባለፈ ሌሎች ሥራዎች የሚሠሩበት እንደኾነም ተናግረዋል። የ2017 በጀት ዓመት ከ2018 እስከ 2022 ዓ.ም ለሚዘልቀው የአምስት ዓመታት የስትራቴጂክ ዕቅድ ለመፈጸም የሚያስችሉ ዝግጅቶች የሚደረጉበት መኾኑንም ገልጸዋል። የ2017 በጀት ዓመት ያለፈው ችግር ጥላውን እንዳያጠላበት የሚደረግበት ዓመት ነው ብለዋል። በመንግሥት እና በፓርቲ ቅንጅት በመፍጠር የተሻለ ሥራ ለመፈጸም ግዴታ የሚገባበት ነው ብለዋል ርእሰ መሥተዳድሩ፡፡
የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ትልቅ ፋይዳ ያለው መኾኑንም አመላክተዋል። ጊዜን በመሻማት የተሻለ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት። ዕቅዳቸውን በምክር ቤት አጽድቀው ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅታቸውን መጨረሳቸውንም ተናግረዋል። የክልሉን ርዕይ የሚያሳይ ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል። ፍኖተ ካርታው ችግሮችን እና ጥንካሬዎችን በመለየት መልካም ሥራዎችን ለመሥራት እንደሚያስችልም አመላክተዋል።
የታቀደው ዕቅድ የቁጭት ዕቅድ ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ከችግር በመውጣት ስኬታማ ደረጃ ላይ ለመድረስ መሥራት ይገባል ነው ያሉት። በከፋ ችግር ውስጥ ቆይተው በሠሩት ሥራ ስኬታማ ከኾኑ ሀገራት ተሞክሮ መውሰድ እንደሚገባም አመላክተዋል። በበጀት ዓመቱ በእያንዳንዱ ቦታ በመግባባት ውጤታማነት የሚረጋገጥበት ነው ብለዋል። የክልሉን የጸጥታ ችግር በማስተካከል እና የውስጥ አቅምን በመጠቀም ሕዝብን ከችግር ለማላቀቅ መሥራት ይገባል ነው ያሉት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!