በምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ እና ፍኖተ ሰላም ከተማ አሥተዳደር የኮሌራ በሽታ መከሰቱን የዞኑ ጤና መምሪያ ገለጸ።

12

ባሕር ዳር: ሐምሌ 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎጃም ዞን ጤና መምሪያ ምክትል ኅላፊ መዝገቡ ውቤ እንደተናገሩት ሁለት የቡሬ ከተማ ነዋሪዎች እና አንድ የፍኖተሰላም ከተማ ነዋሪ ላይ በተደረገ ምርመራ ሶስቱም በኮሌራ በሸታ መያዛቸው ተረጋግጧል። ታካሚዎች አፋጣኝ ሕክምና እንዲያገኙ በመደረጉ ከበሽታው እያገገሙ መኾናቸው ተገልጿል።

የኮሌራ በሽታ የምግብ እና ውኃ መበከል በሚያስከትለው አጣዳፊ ተቅማጥ እና ትውከት የሰውነት አቅምን በማዳክም በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሞት የሚዳርግ በሽታ ነው ብለዋል ምክትል መምሪያ ኅላፊው። በሽታውን የመከላከል ሥራ ላይ ቅድሚያ በመስጠት እና የሕክምና መሳሪያዎችን በማሟላት በሽታው እንዳይሰራጭ በቅንጅት እየተሠራ ስለመኾኑም ተናግረዋል።

ከታካሚዎች ጋር ቅርበት የነበራቸው ሰዎች ላይ አሰሳ በማድረግ በሽታው ወደ ሌሎች ሰዎች እንዳይዛመት የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እየተከናወኑ መኾኑንም ነው አቶ መዝገቡ መናገራቸውን ከምዕራብ ጎጃም ዞን ኮሙኒኬሽን መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በፍኖተ ሰላም ጠቅላላ ሆስፒታል የወረርሽኝ እና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከል እና መቆጣጠር ባለሙያ አቶ አበባው አዲስ ኀብረተሰቡ የመጸደጃ ቤትን በአግባቡ በመጠቀም፣ የመመገቢያ እቃዎችን በንጹህና በመያዝ እና ምግብን በጥንቃቄ በማስቀመጥ ከኮሌራ በሽታ ራሱን እንዲጠበቅ አሳስበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ዕቅድ ብቻውን ዋጋ የለውም፣ ለዕቅድ አፈጻጸም ሥነ ምግባር ያስፈልጋል” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Next article“የ2017 በጀት ዓመት ያለፈው ችግር ጥላውን እንዳያጠላበት የምናደርግበት ዓመት ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ