“ዕቅድ ብቻውን ዋጋ የለውም፣ ለዕቅድ አፈጻጸም ሥነ ምግባር ያስፈልጋል” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

42

ባሕር ዳር: ሐምሌ 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ እና መካከለኛ መሪዎች የ2016 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ መድረክ እየተካሄደ ነው። በመድረኩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬን ጨምሮ ከፍተኛ መሪዎች ተገኝተዋል።

በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ዕቅድ ታላቅ የመግባቢያ መሣሪያ ነው ብለዋል። ዕቅድ የማያቅድ ተቋም ስኬታማ ሥራ መሥራት እንደማይችል ነው ያመላከቱት። በክልሉ የታቀደው ዕቅድ የክልሉን ሃብት የሚያሳይ፣ የሌለውን የሚያመላክት፣ ያለውን ሃብት በምን መልኩ መጠቀም አለብን የሚለውን የሚያመላክት መኾኑንም አንስተዋል።

ክልሉ ከችግር ውስጥ እንዴት እንደሚወጣ፣ የልማት ሥራዎችንም በምን መልኩ መሥራት እንደሚገባም እንደሚያመላክትም ገልጸዋል። የታቀደው ዕቅድ ትልቅ መኾኑንም ተናግረዋል። “ዕቅድ ብቻውን ዋጋ የለውም ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዕቅድ አፈጻጸም ሥነ ምግባር እና መሥዋዕትነት ያስፈልጋል ነው ያሉት። ዕቅዱን ማሳካት ካልቻልን በድህነት ለመኖር ወስነናል ማለት ነው ብለዋል።

እያንዳንዱ አካባቢ ባለው ጸጋ ልክ ገቢውን ማስፋት፣ ኢኮኖሚውን ማሳደግ፣ ሕገወጥነትን መከላከል እንደሚገባውም አመላክተዋል። ብቃትን መሠረት ያደረገ መዋቅር እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። በ2016 በጀት በክልሉ ከጸጥታ ጎን ለጎን በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ያነሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ታላቁ የዓባይ ድልድይ እና የጎርጎራ ፕሮጄክት ታላቅ ትርጉም ያላቸው ሥራዎች መኾናቸውን ተናግረዋል። የዓባይ ድልድይ ከትራንስፖርት እንቅስቃሴው ባለፈ ታላቅ ስጦታ እና የቱሪዝም መዳረሻ እንደኾነም ገልጸዋል።

የጎርጎራ ፕሮጀክት ለየብስ እና ለባሕር ትራንስፖርት የተመቸ፣ የቱሪስት ፍሰትን የሚጨምር እና የቆይታ ጊዜያቸውን የሚያራዝም ታላቅ ፕሮጀክት መኾኑንም አንስተዋል። መልካም ሥራዎችን የበለጠ በማጠናከር፣ ዘላቂ ሰላም በሚያመጡ ሥራዎች ላይ የበለጠ መሥራት ከተቻለ ክልሉ ታላቅ አቅም እና ተስፋ ያለው መኾኑንም ገልጸዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የቦሌ መንገድ የመዲናችን አዲስ አበባ የደመቀ የንግድ እና የዘመናዊ እንቅስቃሴ አገልግሎቶች ማዕከል ነው።”የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት
Next articleበምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ እና ፍኖተ ሰላም ከተማ አሥተዳደር የኮሌራ በሽታ መከሰቱን የዞኑ ጤና መምሪያ ገለጸ።