ዜጎች የቫይረሱ አጠራጣሪ ምልክቶችን በምርመራ በማረጋገጥ ለመከላከል ሥራው ውጤታማነት የበኩላቸውን እንዲወጡ የሰሜን ወሎ ዞን ጤና መምሪያ አስታወቀ፡፡

353

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 26/2012 ዓ.ም (አብመድ) ቫይረሱን ለመከላከል አካላዊ መራራቅን መፍጠርና የተጨናነቁ የትራንስፖርት ጉዞን ማስቀረት የቀጣይ የቤት ሥራዎቹ መሆናቸውንም መምሪያው አስታውቋል፡፡

በመከላከል ሥራው የበጎ ፍቀደኞች ሚና ማደግ እና ግለሰቦች ኃላፊነታቸውን ለመወጣት የሚያደርጉ ጥረት የሚበረታታ እንደሆነም አብመድ ታዝቧል፡፡
በወልዲያ መናኸሪያ ከ16 ቀናት በፊት ጀምሮ ተጓዥችን፣ ደላሎችንና ሹፌሮችን እጃቸውን በማስታጠብ ሥራ የተጠመዱት የ57 ዓመቱ አቶ ተስፋየ ደሳለኝ ‘‘ቫይረሱን ለመከላከል ከዚህ የተሻለ ቦታ የለም’’ ብለው ያምናሉ፡፡

የሚያደርጉት የበጎ አድራጎት ሥራ የዜጎችን ሕይወት መታደግ እንደሚችል ባሰቡ ቁጥር ጉልበታቸውን ከመፈታተን ይልቅ እንደሚያበረታቸው ለአብመድ ተናግረዋል፡፡

አቶ ተስፋየ ቫይረሱ የእያንዳንዱን ዜጋ ጥንቃቄ ስለሚጠይቅ ከበርካታ ሰዎች ጋር የሚገናኙ የመናኸሪያ ሰዎች ከራሳቸው አልፈው ሌሎች እንዲድኑ ትርፍ ባለመጫን እና መስኮት ከፍተው ተሳፋሪ በቂ አየር እንዲያገኝ እንዲያደርጉ እንደሚያስተምሩ ተናግረዋል፡፡

አካላዊ ርቀትን አለመጠበቅ ላይ አሁንም የሚታዩ መዘናጋቶች እንዳሉ ያመለከተት አቶ ተስፋየ ‘‘ቫይረሱ ከሀገራችን ሙሉ በሙሉ ጠፍቷል’’ እስከሚባል ድረስ የበጎ አድራጎት ሥራቸውን እንደሚቀጥሉ ቃል መግባታቸውን ነው የተናገሩት፡፡

በወልዲያ ከተማ በጋራዥ ሥራ ላይ የተሠማሩት አቶ ሰይድ አበበ ‘‘በቫይረሱ ኢትዮጵያ መግባት የተወሰነ መረበሽ አለ’’ ብለዋል፡፡ መረበሹ የፈጠረውን ያክል ግን አካላዊ መራራቅ እና መጨባበጥ አለመቅረቱን ተናግረዋል፡፡
ቫይረሱ የትኛውንም የሰው ልጅ የኑሮ ዘይቤ ተከትሎ የሚመጣ በመሆኑ ለመከላከሉ የሚደረገው ጥረት ሕይወት ለማትረፍ ዋስትና በመሆኑ እንደግለሰብ የራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ደኅንነት ከማስጠበቅ ባሻገር ከጓደኞቻቸውና ጎረቤቶቻቸው ጋር የጋራ መግባባት ላይ እንደደረሱም ተናግረዋል፡፡

የሰሜን ወሎ ዞን ጤና መምሪያ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር አስተባባሪ አቶ አበበ ሲሳይ ዛሬ ለአብመድ እንደተናገሩት በዞኑ እስካሁን በቫይረሱ የተያዘ ሰው አልተገኘም ብለዋል፡፡

ቫይረሱን የመከላከል ሥራውም እንደዞን እና እንደወረዳ በተደራጁ ኮሚቴዎች የመከላከያ ግብዓቶች አጠቃቀም ትምህርትና አቅርቦት ላይ እየሠሩ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ የቫይረሱ ምልክት የነበራቸው ሰዎችን ከየወረዳው በመሰብሰብ በወልዲያ ከተማ ጎንደር በር ጤና ጣብያ ላይ በለይቶ የሕክምና ክትትል ማድረጊያ ሆነው ክትትል እየተደረገላቸው እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡ እስከ ዛሬ በዞኑ በቫይረሱ የተጠረጠሩ 70 ሰዎች ላይም ቫይረሱ እንደሌለባቸው መረጋገጡን አቶ አበበ ተናግረዋል፡፡

በሰሜን ወሎ ዞን ቫይረሱን ለመከላከል የተቋቋሙ ኮሚቴዎች እና ስልጠና ያገኙ የጤና ባለሙያዎች የሚያደርጉት ጥረት የሚደነቅ ቢሆንም ቫይረሱ ለመኖሩ የሚጠቁሙ ሁለት የመመርመሪያ መሳሪያዎች ወልዲያ ቢገቡም ሥራ አለመጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡

የመከላከል ሥራው ውጤታማ እንዲሆን ኅብረተሰቡ አሁንም በጉልህ የሚታዩ የትራንስፖርት መጨናነቆችን እንዲከላከል እና አካላዊ መራራቅን እንዲጠብቅ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

ዜጎች ከቫይረሱ ጋር ተያያዥ የሆኑ ምልክቶች ሲያሳዩ ለጤና ተቋም ደውለውና በጠንቃቄ ወደ ጤና ተቋም ደርሰው በመመርምር ኅብረተሰቡ እንዲረጋጋና ቫይረሱን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ውጤታማ እንዲሆን እንዲያግዙም አቶ አበበ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ቫይረሱ እንዳለባቸው የተጠረጠሩ ሰዎች ቤተሰብ ላይ የሚደረግ ማግለል እንዳይኖር፤ ከውጭ ሀገራት በሚመጡ ዜጎች ላይ የሚስተዋለው መጠራጠር አሳቃቂ እና አሳዳጅ እንዳይሆን የግንዘቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እየሠሩ መሆናቸውንም አቶ አበበ ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ

Previous articleየባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ለከተማዋ ነዋሪዎች የኮሮና ወረርሽኝ መከላከል ግንዛቤ ሲፈጥሩ አረፈዱ፡፡
Next articleየኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል 30 ሺህ በጎ ፈቃደኞች በመዲናዋ ተሰማርተዋል፤ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይም ድጋፍ ተገኝቷል፡፡