ዜጎች ወደ ታይላንድ እና ማይናማር ከሚደረጉ ሕገ-ወጥ ጉዞዎች ራሳቸውን እንዲጠብቁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሳሰበ።

53

አዲስ አበባ: ሐምሌ 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብዩ ተድላ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል። በቅርቡ የተሾሙ አምባሳደሮች የሀገራቸውን ጥቅም ለማስከበር ቃለ መሃላ ፈጽመዋል። ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴም ለተሿሚዎቹ ሀገራዊ አደራ ሰጥተዋቸዋል ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትሩ አምባሳደር ታየ አፅቀሥላሴ ለተሿሚ አምባሳደሮቹ ሀገርን ማገልገል ትልቅ እድል በመኾኑ ኀላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ማሳሰባቸውንም አንስተዋል። ቃል አቀባዩ በቅርቡ በአዲስ አበባ የተደረገው የፋይናንስ ጉባኤን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ ለታዳጊ ሀገራት አማራጭ የፋይናንስ መፍትሄዎችን ያመላከተ እና የአዲስ አበባን ስም እና ዝና ያጎላ እንደነበር አንስተዋል። ጉባኤው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ፣ ዲፕሎማሲያዊ አጋርነትን እና የገፅታ ግንባታ ጥቅሞችን ያመጣ ነው ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አምባሳደር ታየ አፅቀሥላሴ በግሪክ ባደረጉት ጉባኝት በሀገሪቱ የኢትዮጵያን ቆንስላ ከፍተዋል። ሚኒሰትሩ በጣሊያንም ጉብኝት አድርገው በኢትዮ-ጣሊያን የንግድ ፎረም ላይ እንደተሳተፉም ጠቁመዋል። ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው ወደ ታይላንድ እና ማይናማር በሕገ-ወጥ መንገድ የሚጓዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨምሩን እና ይህም ለዜጎቻችን አስቸጋሪ ሁኔታ ፈጥሯል ብለዋል። በሀገራቱ ዜጎቻችን ለከፍተኛ ስቃይ ተጋልጠዋል ነው ያሉት።

ችግሩን ለመቅረፍ በጃፓን በሚገኘው ኢምባሲ በኩል ወደ ሀገራቸው የመመለስ ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት። ዜጎች ከመሰል ሕገ-ወጥ ዝውውር ራሳቸውን እንዲጠብቁም ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ጥሪ አቅርቧል። ቃል አቀባዩ አምባሳደር ነብዩ ተድላ የኢትዮ-ሶማሊ ግንኙነትን በሚመለከት የሚሰነዘሩ እና የሁለቱን ሀገራት ታሪካዊ ግንኙነት የማይመጥን መግለጫዎች ብናስተውልም ጠቃሚ አይደለም በሚል ዝም ብለን ቆይተናል ብለዋል።

የኢትዮጵያን ስም የሚያጎድፉ ጉዳዮች ቀጥለዋል ያሉት ቃል አቀባዩ እንደ ሀገር በደራሽ ጉዳዮች ሳንወሰን በዘላቂ ውይይት ልዩነቶችን ለመፍታት ጥረቶች ይቀጥላሉ ነው ያሉት።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

ዘጋቢ፦ አንዷለም መናን

Previous articleፈለገ ሕይዎት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ነጻ የዐይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ጥገና ህክምና እንደሚሰጥ አስታወቀ።
Next article“የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ዜጎችን ታሳቢ በማድረግ ሀገራዊ ዕድገትን በሚያስቀጥል አግባብ በጥብቅ ቁጥጥር የሚተገበር ነው” አሕመድ ሺዴ