
ባሕር ዳር: ሐምሌ 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የፈለገ ሕይዎት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከነሐሴ 25 እስከ ነሐሴ 29/2016 ዓ.ም ድረስ ነጻ የዐይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ጥገና ሕክምና እንደሚሰጥ አስታውቋል።
የፈለገ ሕይዎት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከኤች.ሲ.ፒ. ኪዩር ብላይንድነስ ጋር በመተባበር ለ12ኛ ጊዜ ከነሐሴ 25 እስከ 29/2016 ዓ.ም ድረስ ነጻ የዐይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ጥገና ሕክምና እንደሚሰጥ አስታውቋል።
በሆስፒታሉ የዐይን ሕክምና ክፍል አሥተባባሪ ተስፋዓለም ጋሻው እንዳሉት ሆስፒታሉ ባለፉት ተከታታይ 11 ጊዜያት 11 ሺህ 500 ለሚኾኑ ታካሚዎች የነጻ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት ሰጥቷል።
ለ12ኛ ጊዜ ከነሐሴ 25 እስከ ነሐሴ 29/2016 ዓ.ም የዐይን ሞራ ግርዶሽ ችግር ያለባቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ለመታደግ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
በመኾኑም፦
👉 ከሐምሌ 29 እስከ ሐምሌ 30/2016 ዓ.ም በመራዊ ከተማ፣
👉 ነሐሴ 05/2016 ዓ.ም በአርብ ገበያ ከተማ፣
👉 ነሐሴ 11/2016 ዓ.ም በአንበሳሜ ከተማ፣
👉 ነሐሴ 12/2016 ዓ.ም በሐሙሲት ከተማ፣
👉 ከነሐሴ 18 እስከ ነሐሴ 19/2016 ዓ.ም በአዴት ከተማ፣
👉 ከነሐሴ 18 እስከ ነሐሴ 23/2016 ዓ.ም በባሕር ዳር ፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የልየታ ሥራ ስለሚሠራ በተጠቀሱት ቦታዎች በመገኘት እና በመመርመር የእድሉ ተጠቃሚ መኾን እንደሚችሉ ተገልጿል። በዚህ ዙር 500 ታካሚዎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ይኾናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የዐይን ሞራ ግርዶሽ የብርሃን ማሳለፊያ ሌንስ ብርሃን የማሳለፍ አቅም ሲደክም የሚፈጠር ነው። በዋናነት በዕድሜ መጨመር ምክንያት የሚከሰት ሲኾን በመመታት፣ በሰኳር እና ተያያዥ ችግሮች ምክንያት ሊከሰት እንደሚችል ነው አሥተባባሪው የገለጹት።
የዐይን ሞራ ግርዶሽ እይታን የሚቀነስ እና የዐይነ ስውርነትን የሚያስከትል ቁጥር አንድ ምክንያት ተደርጎ ይወሰዳል። ቀዶ ጥገና ደግሞ ዋነኛው መፍትሄ እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ችግሩ እየጨመረ በመምጣቱ ሕክምናው ከመደበኛ ሕክምና ባለፈ በዘመቻ መንገድ እየተሰጠም ይገኛል ተብሏል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!