
ባሕር ዳር: ሐምሌ 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ወይዘሮ ዓለም ፈቃዱ በባሕርዳር ዙሪያ ባሉ ገጠራማ አካባቢዎች ይኖራሉ፡፡ እኝህ እናት ትዳር ከመሰረቱ ዓመታት ተቆጥረዋል። ነገር ግን በፈለጉት ጊዜ ወልደው ለመሳም አልቻሉም። ነገር ግን ከብዙ ድካም በኋላ ጎጇቸውን ሊያሞቅ፤ ወግ እና ማዕረጋቸውን ሊያደምቅ የሚችል ስጦታ አገኙ፤ ጸነሱ። ወይዘሮዋ ለረዥም ጊዜ ሲመኙት የነበረ ጉዳይ ነበር እና ደስታቸው ወደር አልነበረውም።
ይህ ልጅ ለወገኑ መኩሪያ ይኾን ዘንድ ከወላጆቹ ባለፈ ዘመድ አዝማድ የሚጠብቀው ብስራትም ነው። ለምን ቢሉ ከሞላው ከተረፈው ከዚያ ቤት ወራሽ ብሎም ዘር አስቀጣይ ይፈለጋል እና ነው፡፡ ወይዘሮ ዓለም ብስራቱን ለወዳጅ ዘመድ ሳይናግሩ ሦስት ወራቶች ቢቆጠሩም እርግጥ መኾኑ በመታወቁ ጉዳዩን ለቅርብ ዘመዶቻቸው ነገሩ፤ ሁሉም ደስታውን ገለጸ፡፡
ይሁን እንጅ ይህ ልጅ በሚገባ የህክምና ክትትል አግኝቶ ይወለድ ዘንድ ከወላጆቹ በተጨማሪ የቤተሰብ የወዳጅ የዘመድ ፍላጎት ቢኾንም በአካባቢው የተከሰተው የጸጥታ ችግር አላላውስ አለ፡፡ ይህ ጉዳይ እያደር እየዋለ ሲሄድ ወይዘሮ ዓለም የህክምና ክትትል ባለማድረጋቸው ችግሮች መከሰት ጀመሩ፡፡
የነበሩትን ችግሮች ሲነግሩን የራስ ምታት፣ ብዥታ፣ እጅ እና እግራቸው ላይ ማበጥ፣ አይናቸው ቢጫ መምሰል፣ መስበክ እና ማንቀጥቀጥ ይታይባቸው ነበር፡፡
ይህ የጤና ችግር ራሳቸውንም ተስፋ የጣሉበትንም ልጅ እንዳያሳጣቸው ከሁለት አጣብቂኝ አንዱን መምረጥ ነበረባቸው እና ቤታቸው ቁጭ ብለው ችግሮችን ከሚቀበሉ ወደ ህክምና አምርተው የሚመጣውን ለመቀበል በጸጥታ ችግር አልፈው በእግራቸው ተጉዘው ባሕርዳር ደርሰው የጤና ምርመራ አደረጉ፡፡
ወይዘሮ ዓለም ባደረጉት ምርመራ በእርግዝና ምክንያት የሚከሰት ግፊት እንዳለባቸው እና ይህም በጊዜው ባለመታከሙ ያስከተለው ችግር እንደኾነ ተነገራቸው። ነገር ግን ክትትል አድርገው ተስፋ የተጣለበትን ልጃቸውንም ራሳቸውንም መታደግ እንደተቻሉ ነው የነገሩን፡፡
በእናቶች እና ሕጻናት የማኅጸን እና ጽንስ ስቴሻሊስት ዶክተር ባዘዘው ፈቃዴ ወይዘሮ ዓለም እና መሰል እናቶች ያጋጠማቸው በእርግዝና ወቅት ከሚከሰቱ ችግሮች ውስጥ አንዱ የኾነው የደም ግፊት እንደኾነ ተናግረዋል፡፡ በአንድ የእርግዝና ጊዜ ላይ ባለች እናት በቅድመ ወሊድ ጊዜ ከሚታዩ ነገሮች አንዱ የደም ግፊት እንደኾነም አስረድተዋል፡፡
ይህ የደም ግፊት ሊመጣ የሚችለው ከአምስት ወር በኋላ ኾኖ ከወሊድ በኋላ የሚጠፋ የግፊት ዓይነት እንደኾነ ነው የሚገልጹት፡፡ ዶክተር ባዘዘው ይህም በእርግዝና ወቅት ከሚከሰቱ ሦስት ገዳይ በሸታዎች ውስጥ አንዱ ስለመኾኑ ገልጸው ይህ ችግር ከ100 ሴቶች ውስጥ በ10 ሴቶች ላይ ይከሰታል ተብሎ ይገመታል ብለዋል፡፡
ከአጋላጭ ጉዳዮች ጋር በተገናኘ ብዙ ጊዜ እድሜያቸው የገፋ ከኾነ፣ ከእርግዝናዋ በፊት በተለያዩ በሽታዎች ተጠቂ ከኾነች ይህም የቆየ የግፊት፣ የኩላሊት፣ የስኳር በሽታ ችግር ያለባቸው ሴቶች ለዚህ ግፊት ተጋላጭ የመኾን ዕድላቸው ከፍ ያለ ስለመኾኑ ተናግረዋል፡፡ አንዳንድ ሴቶች ያረገዙት መንታ ከኾነ ደግሞ ለዚህ ችግር የመጋለጥ ሁኔታው ከፍ ሊል እንደሚችል ዶክተር ባዘዘው አስገንዝበዋል፡፡
ከዘረመል ጋር በተገናኘ ጥቁር ሴቶች ከነጮቹ በተለየ ለዚህ ግፊት ተጋላጭ እንደሚኾኑ አብራርተዋል፡፡ የሰውነት ያላግባብ ውፍረትም ኾነ መቀነስ ለዚህ ችግር እንደሚያጋልጥ ነው ያስረዱት፡፡ ከዚህ ህመም ጋር ተያይዞ የሚመጡ ችግሮችን ስናይ ግፊቱ በመጨመሩ ምክንያት በጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ፣ ራስን መሳት እና ለህልፈት ሊዳርግ ይችላል፡፡ ኩላሊት፣ ጉበት እና መሰል የሰውነት ክፍሎች ሥራ እንዲያቆሙ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ልጁ ያለቀኑ እንዲወለድ አለያም ልጅ ሆድ ውስጥ እንዲጠፋ ሊያደርግ የሚችልበት ሁኔታ ስለመኖሩም ዶክተር ባዘዘው አስገንዝበዋል፡፡ በእርግዝና ወቅት የመድማት ችግርን ሊያስከትል የሚችልበት ሁኔታ ስለመኖሩም ገልጸዋል፡፡
ችግሩን ለመከላከል አስቸጋሪ ቢኾንም አንዲት ሴት የቅድመወሊድ ክትትል እንድታደርግ ዕድል የሚሰጥ በመኾኑ የቅድመ ወሊድ ክትትትል እንድታደርግ የሚደረገውም ይህን ችግር ለመከላከል እንደኾነ ነው የነገሩን፡፡ አንዲት ሴት የቅድመ ወሊድ ክትትል እንድታደርግ የሚደረገው ምልክቱ ሳይታይ የደም ግፊቷ ጨምሮ ሊኾን ስለሚችል ነው ብለዋል ዶክተር ባዘዘው፡፡
በምርመራው አጋላጭ የኾኑ ነገሮችን እና ተያይዘው የሚመጡ ችግሮችን ለመቆጣጠር ያስችላል፤ ስኳር እና ሌሎች የጤና ችግር ያለባት ሴት ችግሩ ሳይቀንስ እንዳታረግዝ አርግዛም ከኾነ ለማከም እና መፍትሄ ለመስጠት ምርመራው ወሳኝ መኾኑን ነው ያስገነዘቡት፡፡ ግፊት ያላት ሴት ምልክቶችን ላታሳይ ትችላለች ያሉት ዶክተር ባዘዘው ለዚህም ነው ሴቶች የቅድመ ወሊድ ከትትል ማድረግ አለባቸው የሚባለው ብለዋል፡፡
ግፊቱ እየጨመረ ሂዶ የተወሳሰበ የእርግዝና ጊዜ ከደረሰ ግን ምልክቶች እንደሚታዩ ነው የነገሩን፡፡ በተለይም ከፍተኛ የኾነ በማስታገሻ የማይመለስ የራስ ምታት፣ አንድ ነገር ሁለቱ ኾኖ መታየት፣ ግፊቱ ኩላሊት ላይ ከፍ ያለ ከኾነ የሰውነት ማበጥ፣ የሽንት መጠኑ እየቀነሰ መሄድ ፣ ጉበት ላይ ከኾነ አይን ቢጫ መምሰል፣ ራስን ማሳት እና ማንቀጥቀጥ እንዲሁም ተደጋጋሚ ማስመለስ፣ ጉበት አካባቢ በተለምዶ ልባችን የምንለው አካባቢ የህመም ስሜት መኖር ከምልክቶቹ ውስጥ ጥቂቶቹ ስለመኾናቸው ነግረውናል፡፡
ዶክተር ባዘዘው በእርግዝና ጊዜ ያለች ሴት የግድ የቅድመ ወሊድ ክትትል ማድረግ እንዳለባት ብለዋል። ይህ ሳይኾን ከቀረ በልጁም ላይ ኾነ በእናት ላይ ከፍ ያለ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ታውቆ ምርመራ ማድረግ ተገቢ እንደኾነ አሳስበዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!