
ባሕር ዳር: ሐምሌ 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ሸዋ ዞን አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማሥተባበሪያ ጽሕፈት እንዳስታወቀው በ2016 በጀት ዓመት 23 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ከክረምት ጋር በተያያዘ ሊከሰት የሚችል የአደጋ ተጋላጭነትን ለማስቀረት የቅድመ መከላከል ሥራ ተከናውኖል፡፡
የጽሕፈት ቤቱ ኅላፊ አበባው መሰለ እንዳሉት የቅድመ ጥንቃቄ ሥራ ቢከናወንም በዞኑ በ5 ወረዳዎች ላይ የመሬት መንሸራተት አደጋ ተከስቷል፡፡ አደጋው የተከሰተባቸው ወረዳዎች ቀወት፣ ኤፍራታና ግድም፣ መንዝ ቀያ ገብርኤል፣ አንኮበር፣ አንጎለላ እንዲሁም ሞጃና ወደራ ናቸው፡፡
አደጋውን ተከትሎም በቋሚ ተክል፣ በቤት፣ በእንስሳት እና በማኀበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ጉዳት ደርሶል፡፡ የጉዳቱን መጠን ለማወቅ ጥናት እየተሠራ ሲኾን ክስተቱ በታየባቸው አካባቢዎች አስቸኳይ ድጋፍ የማድረስ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አቶ አበባው መሰለ ተናግረዋል፡፡
በዞኑ በሚገኙ 14 ወረዳዎች የመሬት መንሸራተት እንዲሁም በሰባት ወረዳዎች የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነት መኖሩን ያነሱት አቶ አበባው ኀብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነትን ለማስቀረት ደግሞ ቦዮችን እና መፋሰሻዎችን ማጽዳት እንደሚገባ ኅላፊዉ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ብርቱካን ማሞ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!