
ሁመራ: ሐምሌ 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በሁመራ ከተማ አሥተዳደር በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የደም ልገሳ መርሐ ግብር ተካሂዷል። በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በሁመራ ከተማ አጠቃላይ ሆስፒታል የድንገተኛ ቀዶ ጥገና ስፔሻሊስት ዶክተር አደም ሙሐመድ ማኅበረሰቡን ከማገልገል ባሻገር በበጎ አድራጎት ተግባር ላይ በመሳተፍ ለ14ኛ ጊዜ ደም መለገሳቸውን ተናግረዋል፡፡
ዶክተር አደም ደም በመለገሳቸው የአዕምሮ እርካታ እና ደስታ ማግኘት እንደቻሉ ነው የገለጹት፡፡ ወላድ እናቶች በደም እጦት እንዳይሞቱ በሙያቸው ከሚሰጡት አገልግሎት ባሻገር ደም በመለገስ የሰብዓዊነት ድርሻቸውን እየተወጡ እንደሚገኙም ነው ያብራሩት።
እንደ ዶክተር አደም ሁሉ ደም በመለገስ ላይ እያሉ አሚኮ ያገኛቸው የሁመራ ከተማ ነዋሪዎች ሕይዎት የምትሰጥ እናት በደም እጦት ምክንያት መሞት እንደማይገባት በማሰብ ደም እየለገሱ መኾኑን ነግረውናል። ደም በመለገስ የእናቶችን ሕይዎት ለማዳን የበኩላቸውን ኀላፊነት በመወጣታቸው ደስተኛ መኾናቸውንም አንስተዋል።
ደም መለገስ የአዕምሮ ደስታ የሚሰጥ በመኾኑ ሁሉም ሰው ደም በመለገስ ሕይዎት ለምትሰጥ እናት አጋርነቱን ማረጋገጥ አለበት ብለዋል። ደም ለጋሾች ደም በሚለግሱበት ወቅት እንደ ካንሰር፣ ለልብ ሕመም እና ለሌሎች በሸታዎች ተጋላጭ ከመኾን እንደሚታደጋቸው በጎንደር ደም ባንክ ቅርንጫፍ አሥተዳደር ጽሕፈት ቤት ቡድን መሪ ተወካይ ኀላፊ ታደሰ ዳግም ተናግረዋል።
በክልሉ የሰላም እጦት በመኖሩ የደም እጥረት የወላድ እናቶችን ሕይወት እየቀጠፈ ይገኛል ያሉት ተወካይ ኀላፊው በክረምት በጎ አድራጎት ብቻ ሳይኾን በቋሚነት በየ ሦስት ወር ደም በመለገስ የሰብዓዊነት ተግባርን ማስቀጠል ይገባልም ብለዋል። ለተከታታይ ሦስት ቀናት በሚቆየው የደም ልገሳ መርሐ ግብር ከበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች 300 ዩኒት ደም ለመሠብሠብ የታቀደ ሲኾን ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 60 ዩኒት ደም መሠብሠብ እንደተቻለ ተገልጿል።
ዘጋቢ :- ያየህ ፈንቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!