“በኢንዱስትሪ ፓርኮች የቻይና ባለሀብቶችን ተሳትፎ ይበልጥ ለማሳደግ በትኩረት እየሠራን ነው” ዶክተር ፍሰሃ ይታገሱ

26

ባሕር ዳር: ሐምሌ 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በኢንዱስትሪ ፓርኮችና በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና የቻይና ባለሀብቶች ተሳትፎ ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍስሃ ይታገሱ (ዶ.ር) ገልጸዋል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው ይህን ያሉት ከ90 በላይ ቻይናውያን ባለሀብቶችና ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የተሳተፉበት ዓመታዊው የኢትዮ-ቻይና ቢዝነስ ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለበት ወቅት ነው።

ዶክተር ፍስሃ በመላው ሀገሪቱ ደረጃቸውን ጠብቀዉ በተገነቡት ኢንዱስትሪ ፓርኮችና የነፃ የንግድ ቀጣና የቻይናውያን ባለሀብቶች ተሳትፎ ከፍተኛ መኾኑን ገልጸዋል። አሁንም ተሳትፏቸውን ይበልጡን ለማሳደግ የሚያስችል ሀገራዊ የኢኮኖሚ ሪፎርሙን መሰረት ያደረገ ተቋማዊ ሪፎርም መተግበራቸውን ነው የተናገሩት።

በመላው ሀገሪቱ በተገነቡት 13 ኢንዱስትሪ ፓርኮችና እና ድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና የመሰረተ ልማት፣ አንድ ማዕከል አገልግሎትና የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች እንዲሁም የተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ዙሪያ የተሠሩ ሥራዎችን ዶክተር ፍስሃ በፎረሙ አብራርተዋል።

የኢትዮ-ቻይና ቢዝነስ ፎረም ኢትዮጵያ እና ቻይና በንግድ እና ኢንቨስትመንት መስክ ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ መኾኑን ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በፎረሙ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች እና የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት እንዲሁም ከተለያዩ የቻይና ግዛቶች የተውጣጡ ከፍተኛ የመንግሥት እና የቢዝነስ ልዑካን እንደተሳተፉበትም ተገልጿል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ በባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ዘርፍ ያላትን አበርክቶ አጠናክራ መቀጠሏ ተገለጸ።
Next articleበደብረ ብርሃን ከተማ ለሚገኙ ተፈናቃዮች 2 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ።