የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ለከተማዋ ነዋሪዎች የኮሮና ወረርሽኝ መከላከል ግንዛቤ ሲፈጥሩ አረፈዱ፡፡

385

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 26/2012 ዓ.ም (አብመድ) የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ መሐሪ ታደሰ (ዶክተር) ዛሬ ረፋዱን ለከተማዋ ነዋሪዎች በኮሮና ወረርሽኝ እና የመከላከያ መንገዶቹ ዙሪያ ግንዛቤ ሲፈጥሩ አርፍደዋል፡፡ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በመኪና ላይ በተገጠመ የድምጽ ማጉያ እየተዘዋወሩ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ግንዛቤ ሲፈጥሩ አርፍደዋል፡፡

ባሕር ዳር በእንቅስቃሴ ገደብ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ጥረት እያደረገች ቢሆንም በተለይ በውስጥ ለውስጥ መንደሮችና አንዳንድ አካባቢዎች ሰዎች ከቤት ወጥተው በጋራ ሲንቀሳቀሱና ሲዝናኑ ይስተዋላል፡፡
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በግንዛቤ ፈጠራ ቅስቀሳቸው ሰዎች የእንቅስቃሴ ገደቡን እንዲያከብሩ፣ አካላዊ መራረቅን እንዲጠብቁ፣ እጃቸውን አዘውትረው በምክረ ሐሳቡ መሠረት እንዲታጠቡና የንጽሕና መጠበቂዎችን እንዲጠቀሙ አሳስበዋል፡፡

በአንዳንድ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች የሚሰጡ ተገቢ ያልሆኑ ምክሮችን ከመፈጸም ተቆጥበው በጤና ባለሙያዎችና በትክክለኛ የመገናኛ ብዙኃን የሚሰጡ መረጃዎችን መሠረት አድርገው ራሳቸውን ከቫይረሱ እንዲጠብቁም ነዋሪዎችን አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- በቀለ ተሾመ

Previous articleየ85 ዓመቷ ኢትዮጵያዊት አዛውንት ከኮሮና ቫይረስ አገገሙ።
Next articleዜጎች የቫይረሱ አጠራጣሪ ምልክቶችን በምርመራ በማረጋገጥ ለመከላከል ሥራው ውጤታማነት የበኩላቸውን እንዲወጡ የሰሜን ወሎ ዞን ጤና መምሪያ አስታወቀ፡፡