
ባሕር ዳር: ሐምሌ 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ በባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ መስክ ያላትን ተሳትፎ አጠናክራ መቀጠሏን ገልጸዋል። አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በዓለም አቀፍ መድረክ ባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ዘርፍ ውስጥ የላቀ አስተዋጽዖ ስታበረክት የቆየች ሀገር መኾኗን አንስተዋል።
ከአፍሪካ በግንባር ቀደም የመንግሥታቱ ማኅበር አባል እና ቀጥሎም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1945 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሲመሠረት ከመሥራች ሀገራት መካከል አንዷ መኾኗንም ነው የገለጹት። በዓለም አቀፍ መድረክ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳትፎ ስታደርግ መቆየቷን አንስተው፤ በዚህም ከተለያዩ ሀገራት ጋር ያላትን የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲዋን እያጠናከረች መምጣቷን አስረድተዋል።
በተለይ በሰላም እና ጸጥታው ዘርፍ በመንግሥታቱ ድርጅት እንዲሁም በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር በሚመሩ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ላይ በመሰማራት ያላት አስተዋጽዖ እጅግ ሰፊ መኾኑንም አብራርተዋል። በዚህም በጎረቤት ሀገራት ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት እንዲረጋገጥ ከፍተኛ አበርክቶ አድርጋለች ብለዋል። በቀጣናውም ኾነ በአፍሪካ ሰላም እንዲሰፍን እና ልማት እና እድገት እዲሳለጥ የምታበረክተውን አስተዋጽኦ አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።
በሌላ በኩል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ.ር) አነሳሽነት እያከናወነች ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ዕውቅና እየተሰጠው መምጣቱን ገልጸዋል። እንደ ኢዜአ ዘገባ ኢትዮጵያ የምታከናውነውን የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር የማስተዋወቅ ሥራ በስፋት እየተሠራ መኾኑን አምባሳደር ተሰፋዬ ይልማ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የሚተከለውን ችግኝ በተመለከተ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግንዛቤ እንዳለውም አምባሳደሩ ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
