
ባሕር ዳር: ሐምሌ 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በኢትዮጵያውያን የገንዘብ እና የሞራል ተሳትፎ እውን የኾነ ፕሮጀክት ነው፡፡
የአማራ ክልል ሕዝብም ግድቡ አሁን ለደረሰበት ደረጃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። አቶ ፈንታ መስተሰሐል በኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ሲሠሩ በነበሩበት ወቅት የተለያዩ ቦታዎችን የመመልከት እድል ያገኙ ግለሰብ ናቸው። ከተመለከቷቸው አካባቢዎች ውስጥ ደግሞ የዓባይ ወንዝ እና በውስጡ የያዛቸው ጸጋዎች ይገኙበታል። ይህ ለሀገሩ በአዳ ኾኖ የኖረው ሃብት ወደ ልማት መግባቱን ተከትሎ ሕዝባዊ ተሳትፎውን በመቀበል ከቀዳሚዎቹ መካከል ነበሩ። ለ13 ዓመታት ያህል ከሚያገኟት የጡሮታ ገቢ ቦንድ በመግዛት አሻራቸውንም አሳርፈዋል። የተጀመረው ግድብ እስኪጠናቀቅ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው ቃል የገቡት።
በአማራ ክልል የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ድጋፍ አሠባሣቢ እና አሥተባባሪ ምክር ቤት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ተናኘ አበበ በ2016 በጀት ዓመት ለመሠብሠብ ከታቀደው 70 ሚሊዮን ብር 61 በመቶ መከወን ተችሏል ብለዋል። ከ42 ሚሊዮን 859 ሺህ ብር በላይ መሠብሠቡን ነው የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊው የገለጹት። ገቢው የተሠበሠበው ከባለሃብቶች፣ ከመንግሥት ሠራተኞች እና ከተቋማት በቦንድ ግዥ እና በልገሳ መኾኑን ተናግረዋል።
ምንም እንኳ በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር እቅዱን ማሳካት ባይቻልም ከ2015 በጀት ዓመት በ 59 ነጥብ 5 በመቶ ብልጫ እንዳለው ነው የተናገሩት። በክልሉ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የቦንድ ግዥ እና ልገሳ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን በክልሉ ከ1 ቢሊዮን 253 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሠብሠብ ተችሏል ነው ያሉት።
ማኅበረሰቡ ግድቡ እስኪጠናቀቅ ቦንድ በመግዛት እና በተፋሰሱ ላይ አረንጓዴ ልማት ላይ በመሳተፍ ታሪካዊ አሻራውን እንዲያሳርፍ ጠይቀዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!