በአማራ ክልል የተከሰተውን የኮሌራ በሽታ ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ኅብረተሰቡ የራሱን ድርሻ እንዲወጣ ተጠየቀ፡፡

19

ባሕር ዳር: ሐምሌ 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኮሌራ በሽታ በዓይን በማይታዩ ተህዋሲያን አማካኝነት የሚመጣ ሲኾን አጣዳፊ ተቅማጥ እና ትውከት በማስከተል በሰውነት ውስጥ የሚገኝን ፈሳሽ አሟጦ በማስወጣት አቅምን የሚያዳከም በሽታ ነው። አፋጣኝ ሕክምና ካልተደረገለትም በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ለሞት የሚዳርግ በሽታ ነው፡፡

በሽታው በክልሉ ከመጋቢት 27/2016 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ዞን እና ወረዳዎች በስፋት እንደተሠራጨ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት የበሽታዎች እና የጤና ሁኔታዎች ምላሽ አሰጣጥ ባለሙያ ሲስተር ሰፊ ደርብ ገልጸዋል፡፡ ሲስተር ሰፊ እንዳሉት ከመጋቢት 27/2016 ዓ.ም ጀምሮ በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዞን ሦስት ወረዳዎች፣ በደቡብ ወሎ ዞን በደሴ እና ኮምቦልቻ ከተማ እንዲሁም በአርጎባ ብሔረሰብ አሥተዳደር ለሁለተኛ ዙር የኮሌራ በሽታ ወረርሽኝ እንደተከሰተ ተናግረዋል፡፡

በእነዚህ አካባቢዎች የተከሰተውን ወረርሽኝ ከቀበሌ ጀምሮ የጤና ባለሙያዎች እና የሚመለከታቸዉ ባለድርሻ አካላት ባደረጉት ከፍተኛ ርብርብ በአጭር ጊዜ ውስጥ መቆጣጠር እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡ ሲስተር ሰፊ አክለዉም ከሚያዝያ 25/2016 ዓ.ም ጀምሮ በ23 ወረዳዎች በሰሜን ጎጃም፣ በምዕራብ ጎጃም ፣ በጎንደር ከተማ፣ በማዕከላዊ ጎንደር፣ በሰሜን እና በደቡብ ጎንደር ኮሌራ በሽታ በስፋት እንደተሠራጨ ገልጸዋል፡፡

ከእነዚህ ውስጥ የስምንት ወረዳዎችን የበሽታ ሥርጭት በአጭር ጊዜ መቆጣጠር እንደተቻለ የገለጹት ባለሙያዋ በአስራ አምስቱ ወረዳዎች ሥርጭቱ እንደተስፋፋ ነው የተናገሩት ፡፡ ሲስተር ሰፊ 26 የሕክምና ማዕከላትን በማቋቋም፣ የጤና ባለሙያዎችን በማሠማራት፣ ግብዓቶችን በማሟላት፣ በተለያዩ ሚዲያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ መልእክቶችን በማስተላለፍ እና በአጠቃላይ ቅንጅታዊ አሠራርን በመከተል በሽታውን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡

በሽታዉ በዋናነት በተበከለ ውኃ እና ምግብ ፣ ከሕመምተኛ ወደ ጤነኛ ሰዉ በንክኪ ይተላለፋል ያሉት ሲስተር ሰፊ ኅብረተሰቡ የግል እና የአካባቢ ንጽሕናን በመጠበቅ፣ ንጽሕናዉ የተጠበቀ ውኃን በመጠቀም እንዲሁም ምግብን አብስሎ በመመገብ በሽታውን መከላከል እንደሚችል ነው የተናገሩት፡፡

በተጨማሪም ከክረምት ወቅት ጋር ተያይዞ ጎርፍ በስፋት ስለሚኖር የምንጠቀመው ውኃ፣ አልፍ አልፎ የቧንቧ ውኃም ቢኾን የመበከል አደጋ ስለሚያጋጥም ውኃን በኬሚካሎች አክሞ እና አፍልቶ በመጠቀም በሽታውን በቀላሉ መከላከል እና መቆጣጠር እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ የበሽታዉ ምልክቶች ከታዩ በአካባቢ በሚገኙ ጤና ተቋማት በመሄድ የባለሙያ ድጋፍ እና የሕክምና አገልግሎት ማግኘት ወሳኝ እንደኾነም ነው የገለጹት፡፡ ሲስተር ሰፊ አክለውም በሽታዉ በተከሰተባቸዉ አካባቢዎች የጤና ተቋማት ባይኖሩ እና ለሚመለከታቸዉ የጤና ባለሙያዎች ማድረስ ባይቻል በክልሉ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ነጻ የስልክ መስመር 6981 በመደወል መረጃ መስጠት እንደሚቻልም አሳስበዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleያልተገባ የንግድ ሥርዓት በተከተሉ አካላት ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።
Next article“የማክሮ ኢኮኖሚ ለውጡን በቁንጽል ሳይሆን በምልዐት መመልከት ይገባል። በመደመር ዕሳቤያችን ለሀገር ልማት ምን መደረግ እንዳለበት በጥልቀት መዝነን አስቀምጠናል። ዓላማችን የኢትዮጵያን ብልጽግና ማረጋገጥ ነው።