ያልተገባ የንግድ ሥርዓት በተከተሉ አካላት ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

127

ባሕር ዳር: ሐምሌ 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የተደረገውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ ፖሊሲ ለውጥ ምክንያት በማድረግ ያልተገባ የንግድ ሥርዓት በተከተሉ አካላት ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ አስታውቋል።

የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል። መግለጫውን የሰጡት የቢሮው ምክትል ኀላፊ ብዙዓለም ግዛቸው መንግሥት የገበያ ሥርዓቱን ለማዘመን እና የኑሮ ውድነቱን ለማሻሻል በርካታ ሥራዎችን መሥራቱን ገልጸዋል።

መንግሥት ዘላቂ ልማትን እና ዕድገትን ለማረጋገጥ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ሲያደርግ መቆየቱን የተናገሩት ምክትል ኀላፊው በተሠሩት ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ለውጦች መገኘታቸውን ገልጸዋል። የፋይናንስ አቅምን የሚያሳድጉ፣ ብዝኃ ኢኮኖሚን የሚያሰፉ፣ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን በጥራት እና በፍጥነት ማጠናቀቅ፣ በግብርናው ዘርፍ መዋቅራዊ ሽግግር እንዲኖር እና ምርታማነት እንዲጨምር መሠራቱን አንስተዋል።

በተሠራው ሥራ 40 በመቶ ደርሶ የነበረውን የኑሮ ውድነት ወደ 20 በመቶ ማውረድ መቻሉንም ተናግረዋል። በንግድ ሥርዓቱ ውስጥ ማነቆ የነበሩ አሠራሮችን በማዘመን፣ የኦንላይን የንግድ ፈቃድ አገልግሎት እንዲሰጥ በማድረግ በኩል ጥሩ ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል። በክልሉ ከ406 ሺህ በላይ የሚኾኑ ዜጎች በኦንላይን ሥርዓት እንዲጠቀሙ ማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል።

ለውጭ የሚቀርቡ ምርቶችን ለባለሃብቶች ክፍት በማድረግ አበርክቶው እንዲያድግ መደረጉንም አስታውቀዋል። ክልሉ ለውጭ ገበያ በሚቀርቡ በጥራጥሬ እና በቅባት ሰብሎች ግንባር ቀደሙን ደረጃ እንደሚይዝም ተናግረዋል። አስመጭ እና ላኪዎች የሚፈልጉትን የውጭ ምንዛሬ የማያገኙበት፣ የገበያ ሥርዓቱ ለጥቁር ገበያ የተጋለጠበት፣ የኮንትሮባንድ እና ሕገወጥ ንግድ መስፋቱን ያነሱት ምክትል ኀላፊው ችግሩን ለማስተካከል የተደረገው የውጭ ምንዛሬ ሥርዓት ማሻሻያ የራሱ የኾነ ፋይዳ አለው ነው ያሉት። ነጻ የውጭ ምንዛሬ ሥርዓት መኖሩ በግብይት ተዋናያን መካከል ፍትሐዊነት፣ ተወዳዳሪነት እና ሕጋዊነት እንዲኖር ያደርጋል ተብሎ እንደሚጠበቅም አንስተዋል።

በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት ይከሰት የነበረውን የሸቀጦች እጥረት እና መጥፋትን ሊከላከል የሚችል እርምጃ ተደርጎ እንደሚወሰድም ገልጸዋል። በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት ሥራቸውን ማስፋፋት ተቸግረው ለነበሩ ባለሃብቶችም ጥቅም እንደሚሰጥ ነው የተናገሩት።

ኢትዮጵያ ያደረገችውን የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ተከትሎ በግብይት ሥርዓቱ ተገቢ ያልኾኑ ፍላጎቶች እና ድርጊቶች መኖራቸውን ተናግረዋል። የተደረገውን የውጭ ምንዛሬ አሥተዳደር ማሻሻያ ምክንያት በማድረግ በንግድ ሥርዓቱ እየተስተዋሉ ያሉ አሉታዊ አዝማሚያዎች መኖራቸውን ነው የገለጹት።
በተለይም በክልሉ በሚገኙ ታላላቅ ከተሞች ከንግድ ሥርዓቱ አሠራር ውጭ ፍላጎቶች መኖራቸውን ተናግረዋል። ከኅብረተሰቡ በሚመጡ መረጃዎች እና ቢሮው በላከው የባለሙያዎች ቡድን ያልተገባ አካሄድ መኖሩን ተረድተናል ነው ያሉት።

ምርት እያለ ምርትን መከዘን እና መደበቅ፣ ያልተገባ የዋጋ ጭማሬ ማድረግ፣ ምርት እያለ የለም ማለት የታዩ አላስፈላጊ አካሄዶች መኾናቸውን ነው የተናገሩት። በተለይም በኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ ከመሸጥ ይልቅ ምርቱን ይዞ የመቆየት ፍላጎት መኖሩንም ገልጸዋል። የክልሉ ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመኾን ችግሩን ለመፍታት እየሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል።

የባለሙያዎች ቡድን ተቋቁሞ ወደ ከተሞች መሄዱንም ተናግረዋል። የተቋቋመው ቡድን መረጃ የመለየት፣ የማስተማር እና እርምጃ የመውሰድ ሥራ ይሠራል ነው ያሉት። የንግድ ሥርዓቱን የሚያስከብሩ ግብረ ኀይሎች እና የቴክኒክ ኮሚቴዎችን ወደ ሥራ የማስገባት ሥራ እየተሠራ መኾኑንም አመላክተዋል።
ባልተገባ የአሠራር ሥርዓት ውስጥ በገቡት ላይ እርምጃ እየወሰዱ መኾናቸውንም ተናግረዋል። እስከ ሐምሌ 24/2016 ዓ.ም በሦስት ከተሞች ላይ 30 የንግድ ድርጅቶችን ማሸጋቸውንም አስታውቀዋል።

ከተደረገው ማሻሻያ ጋር ተያይዞ ያልተገባ ፍላጎት እና ሥርዓት የሚያሳዩ አካላትን ማኅበረሰቡ መረጃ በመስጠት እንዲያጋልጥም ጥሪ አቅርበዋል። ሌሎች ባለ ድርሻ አካላትም ከንግድ እና ገበያ ልማት ጋር በመሥራት በማኅበረሰቡ ላይ የሚደርሰውን ጫና እንዲቀንሱም ጠይቀዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበክልሉ የተከሰተው የሰላም እጦት በመንገድ ግንባታ ላይ ኪሳራ ማድረሱን የሰሜን ጎጃም ዞን ገለጸ።
Next articleበአማራ ክልል የተከሰተውን የኮሌራ በሽታ ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ኅብረተሰቡ የራሱን ድርሻ እንዲወጣ ተጠየቀ፡፡