በክልሉ የተከሰተው የሰላም እጦት በመንገድ ግንባታ ላይ ኪሳራ ማድረሱን የሰሜን ጎጃም ዞን ገለጸ።

14

ባሕር ዳር: ሐምሌ 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ አሰፋ ጥላሁን እንዳሉት ማኀበራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ፖለቲካዊ ፋይዳ ሊያመጡ የሚችሉ አውራ ጎዳናዎች ከ7 ቢሊዮን ብር በላይ ተበጅቶላቸው ሥራቸው እየተሳለጠ ነበር። ይሁን እና ክልሉ በገጠመው የሰላም እጦት ምክንያት ግንባታው በመቋረጡ ዞኑ ለዘርፈ ብዙ ኪሳራ ተዳርጓል ነው ያሉት።

ለአብነትም በ2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ከአዴት ከተማ ተነስቶ ሰከላን ከፈረስ ቤት እንዲያገናኝ ታስቦ እየተገነባ የነበረው 62 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ግንባታ እንደቆመም ዋና አሥተዳዳሪው አብራርተዋል። አቶ አሰፋ ከዱር ቤቴ _ሻውራ_ ደለጎ_መተማ ዮሐንስን የሚያስተሳስር 260 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ በ5 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር እየተገነባ እንደነበርም ጠቁመዋል፡፡ አሁን ግን እንደ ክልል በገጠመው የጸጥታ ችግር ግንባታው ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል ነው ያሉት።

“በተለይ ይህ ሰሜን ጎጃምን በጎንደር በኩል ከሱዳን ጋር እንዲያገናኝ ታስቦ እየተገነባ የነበረው መንገድ በጊዜው ቢጠናቀቅ ይዞት ሊመጣ የሚችለው በረከት ከፍተኛ ነው። ነገር ግን በክልሉ ሰላም በመጥፋቱ እየተገነባ የነበረው መንገዱ አንድ ዓመት ሙሉ ከሥራ ውጭ ኾኗል፤ ስለኾነም በዞኑ ውስጥ ዘርፈ ብዙ ጉዳት አስከትሏል” ሲሉ አቶ አሰፋ ገልጸዋል።

እንደ ዋና አሥተዳዳሪው ገለጻ የመንገድ የግንባታ አውታሮች በመቋረጣቸው በሥራው በቀጥታ በመሳተፍ ላይ የነበሩ ሠራተኞች እንዲሁም ሌሎች በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ በርካታ ወገኖች ለችግር ተዳርገዋል። በጠቅላላው ከሰባት ቢሊዮን ብር በላይ በጀት የተያዘላቸው አውራ ጎዳናዎች በጸጥታ ችግር ምክንያት ግንባታቸው በመቋረጡ ዞኑ ልዩ ልዩ ምጣኔ ሃብታዊ፣ ማኀበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳት እንዲደርስበት ኾኗል።

በመኾኑም የታጠቁ ወንድም እና እህቶች በዓለም ላይ በጦርነት የሚመጣ ሰላም አለመኖሩን ተገንዝበው ልዩነትን በድርድር መፍታት አስፈላጊ ነው ሲሉ ዋና አሥተዳዳሪው ገልጸዋል። በንግድ ሥራ የሚተዳደሩት የዱር ቤቴ ከተማ ነዋሪ የዕድሜ ባለጸጋ ክልሉ አሁን ከገጠመው ግጭት በፊት ባልተመቻቸ መንገድ ነግደው ማትረፍ፣ አቅመ ደካሞችን መርዳት ባይችሉ ቤተሰባቸውን በአግባቡ ያሥተዳድሩ እንደነበር ያስታውሳሉ።

አሁን ግን ዞኑ በገጠመው የሰላም እጦት ምክንያት እየተገነቡ ያሉ መንገዶች በመቆማቸው ተለዋጭ መንገዶችም ስለተዘጉ ነግደው ቤተሰባቸውን መምራት አዳጋች እንደኾነባቸው ተናግረዋል። በሊበን ከተማ የመንግሥት ሠራተኛዋ ወይዘሮ ደግሞ በዞኑ ምቹ የመኪና መንገድ ባለመኖሩ ድንገተኛ ህሙማንን ወደ ከፍተኛ የጤና ተቋማት ማድረስ አልተቻለም ነው ያሉት።

“በቅርቡ እህቴ ወደ ባሕር ዳር ከተማ ሄዳ በቀዶ ሕክምና እንድትወልድ ሐኪም ማዘዣ ቢጽፍላትም በሰላም እጦት መንገዱ በመዘጋቱ በቤቷ ለቀናት አምጣ በባሕላዊ አዋላጅ በመውለዷ የጨቅላውን ህይዎት ማትረፍ አልተቻለም” ሲሉ ተናግረዋል። አስተያዬት ሰጭዎቹ ሀገር እና ሕዝብ በሰላም ውለው እንዲያድሩ ትጥቅ ይዘው እየተዋጉ ያሉ አካላት ጥያቄያቸውን በሰላም እንዲፈቱም ጠይቀዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleቻትቦት ምንድን ነው?
Next articleያልተገባ የንግድ ሥርዓት በተከተሉ አካላት ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።