የአማራ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ በስኬት መጠናቀቁን የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋየ አስታወቁ፡፡

64

ባሕር ዳር: ሐምሌ 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ጉባኤ በስኬት መጠናቀቁን የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋየ አስታውቀዋል፡፡ ምክር ቤቱ በመደበኛ ጉባኤው የክልሉን ወቅታዊ የሰላም፣ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጉዳዮችን በስፋት ተመልክቷል ብለዋል፡፡

የጉባኤውን በስኬት መጠናቀቅ ተከትሎ መግለጫ የሰጡት አፈ ጉባኤዋ የምክር ቤቱ 6ኛ ዙር፣ 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ጉባኤ በተለያዩ ክልላዊ ጉዳዮች ዙሪያ ገንቢ ምክክሮችን አካሂዶ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳርፏል ብለዋል፡፡ ክልሉ ለአንድ ዓመት ከዘለቀው ግጭት ወጥቶ አንጻራዊ ሰላም በበርካታ አካባቢዎች ሰፍኗል ያሉት አፈ ጉባኤዋ የተጀመሩ የሰላም ጥረቶች ዳር እንዲደርሱ የሚያስችሉ ምክክሮች ተካሂደዋል ነው ያሉት፡፡

በክልሉ ሕዝብን ያማረሩ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ በተለይም የፍትሕ ሥርዓቱን በሕዝብ ዘንድ ተዓማኒ ለማድረግ ምክር ቤቱ ምክክሮችን እንዳደረገ አንስተዋል፡፡ አፈ ጉባኤዋ በየደረጃው የሚገኘው የምክር ቤት አባል ቁጥጥር እና ክትትል ማድረግ እንደሚኖርበትም መግባባት ላይ መደረሱን አንስተዋል፡፡

የሕዝቡን የመልማት ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ የመሠረተ ልማት ግንባታ፣ በጀትን በቁጥጥር እና በቁጠባ መጠቀም፣ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን በየደረጃው መፍታት፣ የሕዝብን ጥያቄ እያዳመጡ በየደረጃው ምላሽ መስጠት እና የምክር ቤቱን የክትትል እና ቁጥጥር አቅም ማጠናከር የሚሉ ጉዳዮች መነሳታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

ምክር ቤቱ በመደበኛ ጉባኤው የተለያዩ ደንቦችን እና መመሪያዎችን መርምሮ ማጽደቁን ያነሱት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋየ የክልሉን መንግሥት የ2017 በጀት መርምሮ አጽድቋልም ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በጀታቸው በምክር ቤት የሚጸድቅላቸው የጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የክልሉ ምክር ቤት እና የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ዓመታዊ በጀት መጽደቁንም ጠቁመዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከተምሳሌታዊዋ የምድር ጌጥ፣ ከተፈጥሮ ኀያል ግርማ ሞገሰ ማሳያዋ ምድር ባሕር ዳር ገብተናል” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ
Next articleቻትቦት ምንድን ነው?