
ባሕር ዳር: ሐምሌ 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ጎፋ ዞን፣ ገዛይ ጎፋ ወረዳ፣ ከንች ሻቻ ጎዘዲ ቀበሌ በተከሰተው የመሬት ናዳ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ የሚውል ማድረጉን አስታውቋል።
ሁለት ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው 240 ኩንታል የስንዴ ዱቄት የጎፋ ዞን አስተዳደር መቀመጫ በኾነችው ሳውላ ከተማ በመገኘትም ለዞኑ አሥተዳደር ማስረኩቡን ገልጿል።
በርክክቡ ወቅት የጎፋ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ስላደረገው ድጋፍ አመሥግነዋል። ተጎጂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም እየተደረገ ባለው ጥረት ውስጥ የእርዳታው አስተዋጽኦ የጎላ መምኑንም ነው የገለጹት።
የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ዋና ኃላፊ ሲሳይ ዘሪሁን የድርጅቱን ሠራተኞች በመወከል በተፈጠረው አደጋ የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል። በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦችም መጽናናትን ተመኝተዋል።
የጎፋ ዞን አሥተዳደር የአደጋው ተጎጂዎችን በፍጥነት ለማገዝም ኾነ በዘላቂነት ለማቋቋም የሚደረጉ ድጋፎችን የማሰባሰቡን ሂደት እየመራ ይገኛል ተብሏል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!