በኮሮናቫይረስ የተያዙ 3 ተጨማሪ ሰዎች ተገኝተዋል፤ያገገሙ ሰዎች ደግሞ 4 ደርሰዋል፡፡
በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ የላቦራቶሪ ምርመራ ከተደረገላቸው 89 ሰዎች ውስጥ ሦስት ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ተረጋግጧል፡፡
ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ቫይረሱ የተገኘባቸውን ሶስት ሰዎች ጨምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር 38 ደርሰዋል።
ሦስቱም ግለሰቦች የውጭ አገሮች ጉዞ ታሪክ ያላቸውና ሁሉም በአዲስ አበባ የሚገኙ ናቸው። የመጀመሪያው ግለሰብ የ29 ዓመት ወንድ ሲሆን መጋቢት 10 ቀን ከዱባይ የመጣና በበሽታ ከተያዘ ሰው ጋር የቅርብ ንክኪ የነበረው ነው።
ሁለተኛው የ34 ዓመት ወንድ መጋቢት 23 ከዱባይ የመጣ፣ በማቆያ የነበረና ከበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር የቅርብ ንክኪ የነበረው መሆኑ ታውቋል። ሶስተኛዋ የ35 ዓመት ሴት በመጋቢት 25 ከስዊድን የመጣችና በማቆያ ያለች ናት።
ከዚህ ቀደም በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠው የ85 ዓመት ኢትዮጵያዊ አዛውንት አገግመዋል። እኚህን የ85 አዛውንት ጨምሮ በድምሩ አራት ሰዎች ከቫይረሱ አገግመዋል።
በተጨማሪም ከአዲስ አበበና ከአዳማ 641 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ምርመራ የተደረገላቸው ይገኛል፤ ከዚህም 510 ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው ታውቀዋል።