
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ጉባኤ ሦስተኛ ቀን ውሎ እንደቀጠለ ነው፡፡ ከሰዓት በኋላ በቀጠለው የምክር ቤቱ የመደበኛ ጉባኤ ውሎ የተሻሻለውን የከተማ እና ገጠር መጠጥ ውኃ እና ፍሳሽ አገልግሎቶችን እንደገና ለማደራጀት ተሻሽሎ የወጣ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ አጽድቋል፡፡
የአዋጁ መውጣት አስፈላጊነቱ የሀገሪቷን የውኃ ፖሊሲ እና ስትራቴጂ መሠረት ባደረገ መንገድ ለክልሉ ሕዝብ ደረጃውን የጠበቀ በቂ ውኃ ለማቅረብ ያለመ መኾኑን የክልሉ ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ ኀላፊ ማማሩ አያሌው (ዶ.ር) ለምክር ቤቱ ጠቁመዋል፡፡ በከተሞች የተቋቋሙ የውኃ እና ፍሳሽ አገልግሎቶች ለተቋቋሙለት ከተማ የፍሳሽ ቆሻሻ አነሳስ፣ አሥተዳደር እና አወጋገድ ለማመቻቸት መኾኑን ተናግረዋል፡፡
የተሻሻለው አዋጅ የውኃ እና ፍሳሽ አገልግሎቶችን ደረጃዎች ማሻሻል፣ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ማስፋት እና የመጠጥ ውኃ ተቋማትን ለማሥተዳደር የሚያስችል አደረጃጀትን ለመፍጠር የሚያስችል መኾኑን ዶክተር ማማሩ አያሌው ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም የተሻሻለው የአማራ ክልል ምክር ቤት አደረጃጀት ሥነ ሥርዓት እና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ ለምክር ቤቱ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ የተሻሻለውን የአደረጃጀት ሥነ ሥርዓት እና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ ለምክር ቤቱ ያቀረቡ የሕግ፣ ፍትሕ እና አሥተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ ደሴ ጥላሁን (ዶ.ር) ደንቡን ማሻሻል ያስፈለገው የሕግ አውጪውን የመከታተል፣ የመደገፍ እና የመቆጣጠር አቅም ለማጠናከር ነው ብለዋል፡፡
የሕዝብ ውክልና ያላቸው ምክር ቤቶች የተሰጣቸውን ኀላፊነት እና ሥልጣን በአግባቡ እንዲወጡ ያስችላልም ብለዋል፡፡ የምክር ቤቱ አባላት ለውይይት በቀረቡት ደንብ እና መመሪያዎች ላይ በሰፊው ተወያይተዋል፡፡ የተሻሻለውን የከተማ እና ገጠር መጠጥ ውኃ እና ፍሳሽ አገልግሎቶችን እንደገና ለማደራጀት ተሻሽሎ የወጣውን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ አጽድቋል፡፡
የአማራ ክልል ምክር ቤት አደረጃጀት ሥነ ሥርዓት እና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ አስፈላጊ ግብዓቶች እንዲጨመሩ እና በጠባብ መድረክ ተስተካክሎ ሥራ ላይ እንዲውል በአብላጫ ድምጽ ወሰኗል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!