
ባሕር ዳር: ሐምሌ 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከነሐሴ 1/2016 ዓ.ም ጀምሮ የ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ ለማከናወን የቅድመ ዝግጅት ተግባራትን እያከናወነ መኾኑን የምሥራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ አስታውቋል፡፡
በአማራ ክልል የተከሰተው የሰላም ዕጦት በትምህርት ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡ በምሥራቅ ጎጃም ዞን በግጭቱ ምክንያት የታቀዱ የትምህርት ተግባራትን ማሳካት እንዳልተቻለ የዞኑ ትምህርት መምሪያ ምክትል ኀላፊ ደመላሽ ታደሰ ለአሚኮ ተናግረዋል፡፡
በ2016 የትምህርት ዘመን በሁሉም ደረጃዎች ከ630 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ቢታቀድም በሰላም እጦት ምክንያት ከ8 ሺህ የማይበልጡ ተማሪዎች ብቻ ትምህርታቸውን መከታተል መቻላቸውን ነው የተናገሩት፡፡
ኅብረተሰቡን ለመካስ እና ተማሪዎችን ከደረሰባቸው የሥነ ልቦና ስብራት ለማውጣት ለ2017 የትምህርት ዘመን የቅድመ ዝግጅት ተግባራትን እያከናወነ መኾኑንም መምሪያው አስታውቋል።
የ2017 የትምህርት ዘመንን ውጤታማ ለማድረግ ከ300 በላይ ከሚኾኑ የትምህርት ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት መደረጉን የገለጹት ኀላፊው በ16 ወረዳዎች የትምህርት ንቅናቄ መርሐ ግብር ስለመደረጉም አስታውሰዋል።
በቀጣይም በየቀበሌዎች ውይይት በማድረግ ትምህርትን ለማስቀጠል እየተሠራ መኾኑን ነው ያመላከቱት ። ከነሐሴ 1/2016 ዓ.ም ጀምሮ የ2017 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ ለማከናወን ዝግጅት መደረጉን የተናገሩት አቶ ደመላሽ የምዝገባ ሂደቱን ስኬታማ ለማድረግም ወላጆች፣ መምህራን እና የትምህርት ቤት መሪዎች ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
ትምህርት ሰላምን አጥብቆ የሚሻ ነው ያሉት ኀላፊው የታጠቁ ኀይሎችም ትምህርት ከየትኛውም ፖለቲካ ነፃ መኾኑን በመረዳት የተማሪዎች ምዝገባ ውጤታማ በኾነ መልኩ እንዲከናወን እና የመማር ማስተማር ሥራው እንዲቀጥል ተባባሪ ሊኾኑ ይገባል ነው ያሉት። በ2017 የትምህርት ዘመን በዞኑ ቅድመ መደበኛን ጨምሮ ከ627 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር መታቀዱንም የመምሪያው መረጃ ያመላክታል።
ዘጋቢ፡- መልሰው ቸርነት
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!