የአፈር ማዳበሪያ በበቂ እንዲቀርብላቸው የጎንደር ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደሮች ጠየቁ።

53

ባሕር ዳር: ሐምሌ 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአፈር ማዳበሪያ በበቂ እንዲቀርብላቸው በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የጎንደር ዙሪያ አርሶ አደሮች ጠይቀዋል። ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት የወረዳው አርሶ አደሮች በቂ ማዳበሪያ አልደረሰንም ብለዋል። በተደጋጋሚ የማዳበሪያ አቅርቦት እንደሌለ ሲነገር እንደሚሰሙ የተናገሩት አርሶ አደሮቹ ማዳበሪያው ግን እየደረሳቸው እንዳልኾነ ነው ያስረዱት።

በመንግሥት ማከፋፈያዎች የማዳበሪያ አቅርቦት የለም እንባላለን፤ ከነጋዴዎች ግን ማዳበሪያ ሲሸጥ ይውላል ብለዋል። ከመንግሥት 4 ሺህ ብር ባልሞላ ብር አንድ ኩንታል ማዳበሪያ እንደሚሸጥ እና ከነጋዴዎች በ7 ሺህ ብር እየገዛን ነው ይላሉ። ይህን ማድረግ የሚችሉት አቅም ያላቸው አርሶ አደሮች ብቻ መኾናቸውንም ገልጸዋል።

“የማዳበሪያ አቅርቦት በበቂ እንዲሰጠን ስንጠይቅ ያለንን ጨርሰናል አሁን የለም የሚል ምላሽ ተሰጥቶናል፤ ነገር ግን ማዳበሪያ ከነጋዴ ሲሸጥ እናያለን” ብለዋል። በማዳበሪያ አቅርቦት ነጋዴዎች ሊገቡ እንደማይገባም ተናግረዋል። ለአርሶ አደሮች መሰጠት የሚገባው ማዳበሪያ ለነጋዴዎች እየተሰጠብን ነው በማለትም ቅሬታቸውን ገልጸዋል። በሕገወጥ አሠራር ምክንያት እየተጎዳን ነውም ብለዋል።

ክልል ላይ የማዳበሪያ አቅርቦት ችግር የለም እየተባለ እንሰማለን፤ ከእኛ ለምን አልደረሰም? ሲሉም ይጠይቃሉ። ፍትሐዊ የማዳበሪያ ሥርጭት እንዲኖርም ጠይቀዋል። የምርት መቀነስ ችግር እንዳይገጥም ችግሮች ተስተካክለው ማዳበሪያ በፍጥነት እንዲቀርብላቸው እንደሚፈልጉም ተናግረዋል።

የጎንደር ዙሪያ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አለባቸው ምኅረት የግብርና ተግባራትን ውጤታማ ለማድረግ በቂ የግብዓት አቅርቦት ያስፈልጋል ብለዋል። የግብዓት አቅርቦት ባለፈው የምርት ዘመን ችግር እንደነበር ያስታወሱት ኀላፊው ዘንድሮ የተሻለ አቅርቦት እና ስርጭት እንዲኖር መሠራቱንም ተናግረዋል።

በወረዳው 56 ሺህ 20 ኩንታል ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች ለማቅረብ አቅደው በዞኑ 34 ሺህ ኩንታል እንደተፈቀደላቸውም ገልጸዋል። የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ከደለደለው የማዳበሪያ አቅርቦት ውስጥ 24 ሺህ 123 ኩንታል እንደቀረበላቸውም ተናግረዋል። የቀረበውን ማዳበሪያ በወረዳው ለሚገኙ ቀበሌዎች የማሰራጨት ሥራ መሠራቱንም አስረድተዋል። የጸጥታ ችግሩ ማዳበሪያውን በወቅቱ ለማሠራጨት ፈተና ኾኖባቸው መቆየቱንም አንስተዋል።

የታጠቁ አካላት ማዳበሪያ እንዳትወስዱ ብለውናል በሚል ስጋት አርሶ አደሮች ማዳበሪያ ለመውሰድ መዘግየታቸውንም ገልጸዋል። በዞን የተደለደለው ሁሉም እንዳልደረሰላቸው የተናገሩት ኀላፊው አሁንም እየመጣ ነው፤ ሁሉንም ማሠራጨት ከተቻለ የአርሶ አደሮችን ጥያቄ እንመልሳለን ብለን እናስባለን ነው ያሉት።

እየደረሰ ያለውን ማዳበሪያ በፍትሐዊነት ለማሰራጨት ጥረት እየተደረገ መኾኑንም ገልጸዋል። ኀላፊው በፍትሐዊነት እያሰራጨን ነው ይበሉ እንጂ አርሶ አደሮች ግን በፍትሐዊነት እየደረሰን አይደለም ይላሉ። ኀላፊው ከባለፈው ዓመት ትምህርት ተወስዶ መረጃዎችን መሠረት አድርገን ለአርሶ አደሮች ማዳበሪያ እንዲወስዱ ተደርጓልም ብለዋል። ከተፈቀደው አሠራር ውጭ የተሰጠ ማዳበሪያ የለም፤ ይሄን ደግሞ የሚቆጣጠር ግብረ ኀይል አለ፤ ነገር ግን ማዳበሪያ አውጥተው ለነጋዴ የሚሰጡ ገጥመውናል ነው ያሉት።

በቂ ማዳበሪያ ወስደውም ለመሸጥ ወይም ለመስኖ የሚኾን ማዳበሪያ እንዲሰጣቸው የሚፈልጉ አሉ ብለዋል። አርሶ አደሮች የሚያነሱትን የፍትሐዊነት ችግር ኀላፊው አይቀበሉም፣ እንደ ምክንያት የሚያነሱት ደግሞ ሥርጭቱን የሚቆጣጠር አካል አለ በሚል ነው። በተደራጀ መንገድ በነጋዴዎች ላይ የሚገኝ ማዳበሪያ የለም ብለዋል። ከዞኑ በሚመደብላቸው ማዳበሪያ መሠረት ላልደረሰላቸው አርሶ አደሮች ለማድረስ እንደሚሠሩም ገልጸዋል።

የዞኑ ግብርና መምሪያም በታቀደው ልክ እንደሚያቀርብ ነገሮናል ነው ያሉት። የአቅርቦት ችግር ላይኖር ይችላል በጸጥታ እና በሌሎች ችግሮች ምክንያት በየወረዳው የሚደርሰው በቂ አይይለም ብለዋል። የሚደርሰውን ግን በተሻለ ሁኔታ ለማድረስ እንሠራለን ነው ያሉት። የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ ንጉሤ ማለደ በዞኑ 985 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ለማቅረብ ታቅዶ እንደነበር አንስተዋል።

በክልሉ መንግሥት የተፈቀደው የማዳበሪያ አቅርቦት 580 ሺህ 356 ኩንታል መኾኑንም ገልጸዋል። ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 435 ሺህ 571 ኩንታል ማዳበሪያ ወደ ዞኑ ገብቷል ነው ያሉት። ዞኑ ለወረዳዎች በሚወጣው መሥፈርት መሠረት እንዲሠራጭ እያደረገ መኾኑንም ተናግረዋል።

ወረዳዎች በላኩት ዕቅድ እና ለዞኑ በተፈቀደው የማዳበሪያ አቅርቦት መሠረት በፍትሐዊነት እየተሠራጨ ነውም ብለዋል። የተፈቀደው ማዳበሪያ በጸጥታ ችግር ምክንያት በቶሎ ያለመድረስ ካልኾነ በስተቀር በሥርጭት በኩል ችግር አልገጠመንም ይላሉ። ሥርጭት የሚካሄደው በወረዳ ማዕከል መኾኑንም ገልጸዋል። በዞኑ የማዳበሪያ ፍላጎት መኖሩንም ተናግረዋል። ከወረዳ ማዕከል ወጥቶ በነጋዴዎች እጅ የሚደርስበት ዕድል የለም ይላሉ።

ከዚህ ውጭ ያለ አካሄድ ካለ እናጣራለን ነው ያሉት። አርሶ አደሮች ግን አማራጭ ስናጣ ከነጋዴዎች እየገዛን ነው ብለዋል። ግብዓት በነጻነት ለማቅረብ አለመቻል ሥርጭቱ እንዲዘገይ ማድረጉንም ገልጸዋል። የፍትሐዊነት ጥያቄ እንዳይነሳ ለማድረግ የሚያስችል ሥራ እየሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል።

ማዳበሪያ መውሰድ ለማይችሉ አካላት እንደማይሰጥም ገልጸዋል። አርሶ አደሮች የሚገጥሟቸውን ችግሮች በየደረጃው ለሚገኝ ተቆጣጣሪ አካል ማሳወቅ እንደሚገባቸውም ተናግረዋል። በሚቀርብላቸው መረጃ እና ማስረጃ መሠረት የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወስዱም ገልጸዋል። የግብዓት አቅርቦት ችግር ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም፣ የማዳበሪያ ሥርጭት በፍትሐዊነት ለማድረስ እና ለችግሮች መፍትሔ ለመስጠት እንሠራለን ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሰው ኀይል አለመሟላት፣ በፀጥታ ችግር መኖር እና በውስብስብ ምርመራ ምክንያት ዕቅዱን ማሳካት እንዳልቻለ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ገለጸ፡፡
Next articleየተማሪዎች ምዝገባ ለማከናወን የቅድመ ዝግጅት ተግባራት እየተከናወነ ነው” የምሥራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ