በሰው ኀይል አለመሟላት፣ በፀጥታ ችግር መኖር እና በውስብስብ ምርመራ ምክንያት ዕቅዱን ማሳካት እንዳልቻለ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ገለጸ፡፡

97

የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ጉባኤ ሦስተኛ ቀን ውሎ እንደቀጠለ ነው፡፡ ምክር ቤቱ በሦስተኛ ቀን ረፋድ ቆይታው ተጠሪነታቸው ለምክር ቤቱ የኾኑ ተቋማትን የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸም እና የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድን አዳምጧል፡፡

የአማራ ክልል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም እና የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድን ለምክር ቤቱ አቅርቧል፡፡ የአማራ ክልል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ዋና ኦዲተር አማረ ብርሃኑ (ዶ.ር) የመሥሪያ ቤታቸውን ዕቅድ አፈጻጸም እና የቀጣይ በጀት ዓመት ዕቅድ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡

ዋና ኦዲተሩ በሪፖርታቸው እንዳሉት ተቋማዊ አቅም ግንባታ፣ የኦዲት ሽፋን፣ የኦዲት ጥራት ማረጋገጥ እና የኦዲት ተግባቦትን ማሳደግ የመሥሪያ ቤታቸው የትኩረት አቅጣጫዎች ኾነው መቆየታቸውን አንስተዋል፡፡ በክልሉ ከ2 ሺህ 660 በላይ ኦዲት ተደራጊ መሥሪያ ቤቶች እንዳሉ ያነሱት ዋና ኦዲተሩ 776 ተቋማት የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጣቸው እና ስጋት ያለባቸው ተቋማት ኾነው መለየታቸውን አንስተዋል፡፡

የክልሉ ኦዲት ሥራዎች የክልሉን የልማት ትኩረት አቅጣጫዎች፣ ታላላቅ ፕሮጀክቶች እና የሕዝብ ጥያቄ ያለባቸውን ተቋማት በመለየት ኦዲት እየተሠራ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡ የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤቱን ነጻነት እና ገለልተኛነት ለማጠናከር የሚያስችሉ ስድስት መመሪያዎች መዘጋጀታቸውንም በሪፖርታቸው አንስተዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ የ417 ተቋማትን የፋይናንስ ሕጋዊነት ኦዲት ለመሥራት ታቅዶ 166 ተቋማትን የፋይናንስ ሕጋዊነት ኦዲት መሥራት ተችሏል ያሉት ዋና ኦዲተሩ አፈጻጸሙ በመቶኛ ሲሰላ 40 በመቶ ብቻ ነው ብለዋል፡፡ ክልሉ ከመደበው ዓመታዊ በጀት ውስጥ 50 በመቶውን በኦዲት ለመሸፈን ቢታቀድም 32 በመቶውን መሸፈን ተችሏል ብለዋል፡፡

በክዋኔ ኦዲት ደግሞ 16 የክዋኔ ርእሶችን (መሥሪያ ቤቶች) ተደራሽ ለማድረግ ታቅዶ ስምንት አርእስቶችን ኦዲት ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡ የኦዲት ሽፋንን ለማሳደግ የግል ኦዲተሮችን ተሳትፎ ማጠናከር አስፈላጊ ነበር ያሉት ዋና ኦዲተሩ ዶክተር አማረ ብርሃኑ ለዚህ የሚያግዝ አዋጅ ተዘጋጅቶ በምክር ቤቱ ስለመጽደቁ አስረድተዋል፡፡

ለአዋጁ ማስፈጸሚያ የሚኾን መመሪያ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ እየተገባ እንደኾነም አንስተዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ በአጠቃላይ አስቻይ ሁኔታዎችን ሁሉ በመጠቀም የኦዲት ሽፋንን ከፍ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል ያሉት ዋና ኦዲተሩ የሰው ኀይል አለመሟላት፣ የፀጥታ ችግር መኖር እና አንድ አንድ የኦዲት ሥራዎች ውስብስብ ምርመራን የሚጠይቁ መኾናቸው ዕቅዱን ለመሸፈን ፈተና ኾነው ቆይተዋል ብለዋል፡፡

በቀጣዩ በጀት ዓመትም ተጠንቶ የቀረበውን የሰው ኀይል መመሪያ አጸድቆ ወደ ሥራ በመግባት የተሻለ ሽፋን እና ጥራት ያለው የኦዲት አገልግሎት ለመስጠት መታቀዱንም አንስተዋል፡፡ በ2017 በጀት ዓመት የ285 መሥሪያ ቤቶችን የፋይናንስ ሕጋዊነት ኦዲት ለማድረግ እና 17 የክዋኔ ኦዲት ለማድረግ መታቀዱንም ገልጸዋል፡፡

የምክር ቤት አባላቱም አሉ ያሏቸውን የሽፋን እና የጥራት ውስንነቶች እንዲስተካከሉ አስተያየት በመስጠት ያለፈውን ዓመት አፈጻጸም እና የቀጣዩን በጀት ዓመት ዕቅድ አጽድቀዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አዲስ ተሿሚ አምባሰደሮችን አነጋገሩ።
Next articleየአፈር ማዳበሪያ በበቂ እንዲቀርብላቸው የጎንደር ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደሮች ጠየቁ።