ባሕር ዳር፡ መጋቢት 26/2012 ዓ.ም (አብመድ) የኮሮና ቫይረስ ምርመራ በባሕር እንደሚጀመር የአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡ ኢንስቲትዩቱ ይህንን የገለጸው የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ ቤተ ሙከራውን በጎበኙበት ወቅት ነው፡፡
ኢንስቲትዩቱ ምርመራውን ከመጭው ሰኞ ጀምሮ ለማካሄድ ሙሉ የቤተ ሙከራ ዝግጅት ማጠናቀቁን ነው ያስታወቀው፤ ሁለት ባለሙያዎች ሙሉ ስልጠና ወስደውና ግብዓቶችም ተሟልተው ከነገ በስቲያ ጀምሮ ምርመራ ለማካሄድ ዝግጁ መሆኑን ነው ያመለከተው።
በቅርቡም በጎንደርና ደሴ ተመሣሣይ የምርመራ ሥራ እንደሚጀመር የአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስትዩት አመልክቷል፡፡ በደብረ ብርሃንም የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ለማድረግ ቤተ ሙከራውን ለማሟላት እየተሠራ እንደሆነ አስታውቋል፡፡
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳደር ተመሥገን ጥሩነህ ወረርሽኙን ለመከላል እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለጽ ከመከላከሉ ጎን ለጎን ደግሞ በክልሉ በሚገኙ ሆስፒታሎች ሁሉ ምርመራ ለማድረግ እንዲቻል ጥረቶች መጀመራውን አስታውቀዋል፡፡ የሚያፈልጉ ግብዓቶችን ከፌዴራል መንግሥትና ከውጭ ለማግኘት ጥረት እየተደረገ እንደሆነና በከፊልም በመምጣት ላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ርእሰ መሥተዳድሩ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ባለሀብቶች ወረርሽኙን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ እያደረጉት ያለውን ጥረት አመሥግነዋል፤ ሌሎችም የእነሱን አርዓያነት እንዲከተሉ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ስማቸው እሸቴ