ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች ከ150 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ገለጸ።

23

ባሕር ዳር: ሐምሌ 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ አንዱ ተልዕኮው ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን (“ኤክሥፖርት”) ምርቶችን በማምረት የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማሳደግ ነው፡፡

በ2016 በጀት ዓመት ከአምራች ኢንዱስትሪዎች እና ሆርቲካልቸር ዘርፎች ከተላከው 140 ሺህ 528 ቶን ምርት 150 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ ለአሚኮ ገልጸዋል። ከዚህ ውስጥ15 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር የሚኾነው ገቢ ከሆርቲካልቸር ምርት የተገኘ ነው። በበጀት ዓመቱ የተገኘው ገቢ ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲታይ በ11 ሚሊዮን ዶላር ብልጫ አሳይቷል።

ጠርሙስ እና ብርጭቆ፣ ሶፍት፣ ኦፓል፣ ፕላይ ውድ፣ ችፑድ፣ የተለያዩ የባሕል እና ዘመናዊ አልባሳት ወደ ውጭ ከተላኩት ምርቶች ዋና ዋናዎቹ ናቸው። ቻይና፣ አሜሪ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ስዊድን፣ ኔዘርላንድ ጣልያን፣ ታይላንድ፣ ቬትናም፣ ዱባይ እና ሕንድ ደግሞ የምርቶቹ መዳረሻ ሀገራት እንደኾኑ ተጠቅሰዋል።

ከዚህም ባለፈ ሀገሪቱ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወደ ሀገር ውስጥ ታስገባ የነበሩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ የመተካት ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል። በዚህም በበጀት ዓመቱ 355 አምራች ኢንዱስትሪዎች 77 ዓይነት ምርቶች 564 ሺህ 132 ቶን ምርት በማምረት ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬን ማዳን ተችሏል ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ የአምራች ኢንዱስትሪውን የማምረት አቅም 61 በመቶ ለማድረስ ቢታቀድም በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት የተመረቱ ምርቶችን እና ለኢንዱስትሪው አስፈላጊ ግብዓቶችን ለማቅረብ ባለመቻሉ ግቡን ለማሳካት አልተቻለም ብለዋል። ለግቡ አለመሳካት የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የመፈጸም፣ የማስፈጸም እና ሌሎች ችግሮችም መኾናቸውን አንስተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሀገራዊ ምክክሩ የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎና ሚና ላይ ያተኮረ ምክክር እየተካሄደ ነው።
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አዲስ ተሿሚ አምባሰደሮችን አነጋገሩ።