በሀገራዊ ምክክሩ የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎና ሚና ላይ ያተኮረ ምክክር እየተካሄደ ነው።

19

ባሕር ዳር: ሐምሌ 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌደሬሽን ጋር በመተባበር በምክክሩ ሂደት የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎና ሚና ላይ ያተኮረ ሁለተኛው ዙር ሀገር አቀፍ የምክክር መድረክ በሐዋሳ ከተማ እያካሄደ ይገኛል።

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ (ዶ.ር) በኢትዮጵያ በተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችና በሀሳብ መሪዎች መካከል የሚስተዋሉ መሠረታዊ የኾኑ ልዩነቶችንና ሀገራዊ ችግሮችን በምክክር ለመፍታት በአዋጅ የተቋቋመው ኮሚሽኑ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ሀገሪቱ በሚያጋጥሟት ግጭቶች አካል ጉዳተኞች ግንባር ቀደም ተጎጅዎች በመኾናቸው ችግሮቹን በውይይት ለመፍታት በሚደረገው ሂደት ትርጉም ያለው ተሳትፎ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተናግረዋል። በምክክሩ አካል ጉዳተኞች አጀንዳቸውን ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከማሳወቅ ባሻገር በሂደቱ በባለቤትነት ስሜት መሳተፍ እንደሚገባቸው ኮሚሽነሩ አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አባይነህ ጉጆ በኢትዮጵያ ከ23 ሚሊዮን በላይ የኾኑ የአካል ጉዳተኞች እንደሚገኙ ጠቁመዋል። በሀገሪቱ በሚፈጠሩ አለመግባባቶችና ግጭቶች ሁሉም ማኅበረሰብ ተጎጅ ቢኾንም አካል ጉዳተኞች ግን የከፋ ተጎጂ መኾናቸውን አንስተዋል፡፡
ችግሮችን በምክክር በመፍታት ሂደት የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ እጅግ በጣም አስፈላጊ መኾኑን ጠቁመዋል።

የምክክር መድረኩ ተሳታፊ የአካል ጉዳተኞች ተወካዮች ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ፣ ችግሮችን በዴሞክራሲያዊ ውይይት የመፍታት ባህል እንዲያዳብሩ አሳስቧል። በምክክር መድረኩ ከክልሎች፣ ከከተማ አሥተዳደሮች፣ ከተለያዩ የአካል ጉዳተኞች ማኅበራትና ከአካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን የተወጣጡ ተወካዮች እየተሳተፉበት ይገኛሉ፡፡

የሐዋሳው የአካል ጉዳተኞች የምክክር መድረክ ዛሬና ነገ ይቀጥላል ተብሏል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በፓርኩ ወጣቶችን በማደራጀት የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል” የአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ
Next articleወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች ከ150 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ገለጸ።