
ባሕር ዳር: ሐምሌ 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ በውስጡ ብዙ ጸጋዎችን የያዘ እና ሃብቶቹ ገና ያልተነኩ አካባቢ ነው። በፓርኩ ፈር ዞን አካባቢ የሚገኙ ሃብቶችን በአግባቡ መጠቀም እንዲቻል ወጣቶችን በማኅበር በማደራጀት እና በተናጠል በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ላይ እንዲሰማሩ ማድረግ አንዱ ነው።
ወደ ሥራ እንዲገቡ ከተደረጉበት የሥራ ዘርፎች ውስጥ የንብ ማነብ ሥራ አንዱ ነው። አሚኮ ያነጋገረው ወጣት እንዳለው በአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ አካባቢ 4 ሄክታር መሬት ላይ ከየካቲት 2016 ዓ.ም ጀምሮ በ250 የንብ ቀፎዎች የንብ ማነብ ሥራ እየሠራ ይገኛል። 900 ሺህ ብርም ለሥራው ወጭ ማድረጉንም ወጣቱ ገልጿል። ከአጠቃላይ ቀፎዎቹ ውስጥ ደግሞ 100 የሚኾኑት ዘመናዊ ቀፎዎች ናቸው።
መጀመሪያ ወደ ሥራ እንደገቡ ለ200 ጊዜያዊ ሠራተኞች የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸው እንደነበር ገልጿል። ለንብ ማነብ ሥራው መነሻው ደግሞ ከዚህ በፊት በእጣን እና ሙጫ ሥራ በአገኘው ገቢ መኾኑን ነግሮናል። አካባቢው ጫካ እና ለንብ ማነብ ሥራ ምቹ በመኾኑ ዘርፉን እንደመረጠው ነግሮናል። ወደ ፊትም ጥራት ያለው ማር በማምረት ከአካባቢው ባለፈ በክልል ደረጃ ማር ለማቅረብ ማቀዱን ነው ያስረዳው።
ወጣቶች ተደራጅተው ወደ ሥራ ቢገቡ ራሳቸውን በመለወጥ ፓርኩንም የመንከባከብ እና የመጠበቅ አጋጣሚ ይፈጥራል ብለዋል። የአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ ኀላፊ ሙላው ሽፈራው በፓርኩ ውስጥ እና በፈር ዞን አካባቢ የሚገኙ ጸጋዎችን ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየተሠራ ይገኛል።
ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ 287 ወጣቶችን በማደራጀት በፓርኩ ፈር ዞን በተከለሉ አካባቢዎች በሚገኙ ውኃማ አካላት ላይ በአሳ፣ በሙጫ ልማት፣ በንብ ማነብ ሥራ እንዲሠማሩ ተደርጓል። ወጣቶቹ ሙያዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሚገኙም ገልጸዋል። በእጣን ማምረት ሥራ የተደራጁ ወጣቶች በሚሊዮን ብር የሚገመት ሃብት ማፍራታቸውን ነግረውናል።
ወጣቶቹ በመኖ ልማት ዘርፍ መሰማራት ቢችሉ ዝናብ አጠር እና የመኖ እጥረት በአለባቸው አካባቢዎች በማቅረብ ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻልም አንስተዋል። ፓርኩ ባለው ስፋት መጠን የያዛቸውን ጸጋዎች ማልማት ቢቻል የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል ነው የነገሩን።
የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚነት በይበልጥ ለማሳደግ ከደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ጋር በቅንጅት እየተሠራ ይገኛል።
ዩኒቨርሲቲው በከብት ማድለብ እና በንብ ማነብ ሥራ መሥራት የሚያስችለውን ቦታ በፓርኩ ፈር ዞን ላይ የልየታ ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል። ሌሎች በክልሉ የሚገኙ እንደ ጎንደር፣ እንጅባራ፣ ደብረ ማርቆስ የመሳሰሉ ዩኒቨርሲቲዎች እና ከዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ጋር ፓርኩን በማልማት የማኅበረሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎችን ለመሥራት በዝግጅት ላይ መኾናቸውንም ነግረውናል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!