በዚህ ዓመት የተጀመረው የአብሮነት እና የሀገር ግንባታ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘለቄታዊ ሰላም ለመገንባት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተጠቆመ።

13

ባሕር ዳር: ሐምሌ 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኅላፊ ተሾመ ፈንታው በዘንድሮው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 8 ሚሊዮን 304 ሺህ 679 ሰዎችን ለማሳትፍ ዕቅድ መያዙን ተናግረዋል። በአገልግሎቱም 13 ሚሊዮን የሚጠጋ የኅብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ እንደሚኾን ይጠበቃል ነው ያሉት።

ኀላፊው እንደገለጹት በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ 14 ዓይነት ሥራዎች ይከናወናሉ። ከእነዚህም መካከል የአብሮነት እና ሀገር ግንባታ ተግባራት፣ የመማር ማስተማር፣ የደም ልገሳ፣ የአቅመ ደካማ ቤቶችን መገንባት እና መጠገን እንዲሁም ሌሎችም አገልግሎቶች ይከናወናሉ። የዚህ ዓመት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሁለት የተለያዩ ገጽታዎች እንዳሉት አቶ ተሾመ አብራርተዋል፡፡ ይህም የአብሮነት እና የሀገር ግንባታ አገልግሎት ነው።

ይህ አገልግሎት ከዚህ በፊት እንዳልነበር የሚናገሩት ምክትል ቢሮ ኅላፊው ተሾመ ፋንታው አገልግሎቱ በተለይ የቆየውን የአብሮነት እሴት በማጠናከር በክልሉ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት አወንታዊ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል። የዚህ ዓመት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በዕድሜ የተገደበ አለመኾኑ ሌላው የተለየ ገጽታው ነው። የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሐ ግብር ከተቀረጸ ጀምሮ ወጣቶች ብቻ ሲሳተፉ እንደነበር አቶ ተሾመ አስታውሰዋል፡፡

በዚህ ዓመት ግን ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዕድሜ ገደብ ሊኾን አይገባም በሚል ፍላጎት እና አቅም ያላቸውን በጎ ፈቃደኞች ለማሳተፍ መታቀዱንም ነው ያብራሩት። ይህም የተሳታፊዎችን ቁጥር እንደጨመረው ገልጸዋል። ከዚህ በፊት 5 ሚሊዮን የሚጠጋ ወጣት ይሳተፍ እንደነበር የገለጹት ምክትል ቢሮ ኅላፊው በዚህ ዓመት ከ8 ሚሊዮን በላይ በጎ ፈቃደኞችን ለማሳተፍ መታቀዱን እንደማሳያ አንስተዋል።

ያም ኾኖ ከ65 በመቶ በላይ የሚኾኑት ተሳታፊዎች ወጣቶች መኾናቸውን አቶ ተሾመ ገልጸዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleመድኃኒትነት ያላቸውን ችግኞች በመትከል የአረንጓዴ አሻራ ሥራን በውጤታማነት ለማከናወን እየሠራ መኾኑን ጤና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
Next article38ኛ መደበኛ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ውሳኔዎች