
አዲስ አበባ: ሐምሌ 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ)መድኃኒትነት ያላቸውን ችግኞች በመትከል የአረንጓዴ አሻራ ሥራን በ2016 ክረምት አጠናክሮ እንደሚቀጥል የጤና ሚኒስቴር ገልጿል።
በክረምቱ ውስጥ ከተጠሪ ተቋማቱ ጋር በመተባበር ሚኒስቴሩ ከሚተክላቸው 500 ሺህ ያክል ችግኞች ውስጥ 10 በመቶ የሚኾኑት ለመድኃኒትነት የሚውሉ ችግኞች መኾናቸውን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ተናግረዋል። የጤና ሚኒስትሯ የመድኃኒት ባህሪ ያላቸውን ችግኞች የመትከሉ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ ነው የተናገሩት፡፡
ይህ ሲኾን በአንድ በኩል ትውልዱ ራሱን የሚያድንበት በሌላ በኩል የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚቻልበት ሁነት እንደሚፈጠር ነው ያብራሩት። የጤና ሚኒስቴር በ2016 ዓ.ም የክረምት ችግኝ ተከላ ከተጠሪ ተቋማቱ ጋር በመተባበር ዕቅዱን እንደሚያሳካ አሳውቀዋል።
ዛሬ በአርማወር ሀንሰን የምርምር ማዕከል እና በአለርት ሆስፒታል ለመድኃኒትነት የሚያገለግሉ ችግኞች ተተክለዋል። በግቢው ውስጥም የምግብነት ባህሪ ያላቸው ሌሎች ችግኞችም ስለመተከላቸው ነው የተገለጸው። የአለርት ሆስፒታል ችግኝ በመትከል እና ግቢውን በማስዋብ የታካሚዎች ጭንቀትን መቀነስ የሚያስችል ሥራ መሥራቱ ነው የተብራራው።
አርማወር ሀንሰን የምርምር ተቋም የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የመድኃኒት ዕውቀት በመድኃኒት ኢንዱስትሪው ውስጥ ከፍተኛ ሚና እንዲኖረው ምርምሮችን እየሠራ መኾኑን አሳውቋል።
ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!