በኃይል ወደ ለይቶ ማቆያ የተወሰዱት ኬንያዊ ፖለቲከኛ ከቫይረሱ አገገሙ፡፡

130

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 26/2012 ዓ.ም (አብመድ) በፖሊስ ወደ ለይቶ የሕክምና መከታተያ ተወስደው የነበሩት የኬንያ ፖለቲከኛ ከኮሮና ቫይረስ ሙሉ በሉሙ ማገገማቸው ተገልጧል፡፡

የኮሮና ወረርሽኝ መዛመትን ለመግታት በሚል ኬንያ ከውጭ ሀገራት የሚመለሱ ሰዎች በለይቶ ማቆያ ሆነው የጤናቸውን ሁኔታ እንዲከታተሉ አያደረገች ትገኛለች፡፡ ወረርሽኙ ከተከሰተባት ጀርመን ቆይተው የመጡት በሀገሪቱ ታላቅ ፖለቲከኛ እንደሆኑ የተነገረላቸው ጌዲዮን ሳቦሪ ግን መመሪያውን ለማክበር ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡ እናም በግዳጅ በቁጥጥር ሥር ውለው ለ14 ቀናት ወደ ለይቶ መከታተያ ክፍል ተወስደው ነበር፡፡ የኮሮና ቫይረስ እንዳለባቸው በመረጋገጡም የሕክምና ክትትል ሲደረግላቸው መቆየቱ ታውቋል፡፡

በማቆያ ማዕከል ከገቡ በኋላ ጸጸታቸውን ሲገልጹም “በእኔ ምክንያት ውጥረት በመፈጠሩ ይቅርታ እጠይቃለሁ” ማለታቸውን ዴይሊ ኔሽን ጋዜጣ ዘግቧል፡፡

የኬንያ መገናኛ ብዙኃን የሀገሪቱን የጤና ሚኒስቴር ዋቢ አድርገው እንደዘገቡት ደግሞ ፖለቲከኛው ጌዲዮን ሳቦሪ አሁን ሙሉ በሙሉ ከቫይረሱ አገግመዋል፡፡

የኬንያ ጤና ሚኒስቴር እንደገለጸው አሁን ላይ በሀገሪቱ ካለው የወረርሽኙ ሥርጭት ውስጥ ከ25 እስከ 30 በመቶ የሚሆነው የሌላ ሀገር የጉዞ ታሪክ በሌላቸው ሰዎች ላይ የተከሰተ ነው፡፡ በመሆኑም ሁሉም ዜጋ ራሱን ከመተላለፊያ መንገዶች እንዲጠብቅ መልእክት አስተላልፏል፡፡

ሁሉም ዜጋ ራሱን ከወረርሽኑ እንዲከላከልና እንዳያዛምት ለማድረግም የመከላከያ ቁሳቁስ እያቀረበች ትገኛለች፡፡ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛዎችን አቅራቢዎችም ከ20 የአሜሪካ ሳንቲም ባልበለጠ ዋጋ እንዲሸጡ እየተደረገ እንደሆነ የሀገሪቱ የንግድ ሚኒስቴር ገለጧል፡፡

እስከ ዛሬ መጋቢት 26/2012 ዓ.ም ረፋድ ድረስ በኬንያ 122 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል፤ አራት አገግመዋል፤ አራት ደግሞ ይሕወታቸውን አጥተዋል፡፡

በአስማማው በቀለ

Previous articleበኩር መጋቢት 21-2012 ዓ/ም
Next articleየኮሮና ቫይረስ ምርመራ ሰኞ በባሕር ዳር ይጀመራል፡፡