የማንነት እና ወሰን ጥያቄዎች በዘለቄታዊ መንገድ እንዲፈቱ እየተሠራ መኾኑን ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ አስታወቁ፡፡

63

ባሕር ዳር: ሐምሌ 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ጉባኤ ሁለተኛ ቀን ውሎ እንደቀጠለ ነው፡፡ በምክር ቤቱ መደበኛ ጉባኤ ሁለተኛ ቀን የከሰዓት በፊት ቆይታ የክልሉ መንግሥት የ2017 በጀት ዓመት የልማት እና መልካም አሥተዳደር እቅድ ቀርቧል፡፡

የቀረበውን የክልሉን መንግሥት የ2017 በጀት ዓመት የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሪፖርት ተከትሎ የምክር ቤቱ አባላት ጥያቄዎች እና አስተያየቶችን ሰንዝረዋል፡፡ የምክር ቤቱ አባላት የታቀደውን የልማት እና የመልካም አሥተዳደር እቅድ በመተግበር የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ስልት ካለ እንዲብራራላቸው ጠይቀዋል፡፡

የምክር ቤት አባላቱ በተለይም ክልሉ ያስቀመጣቸውን የልማት እና መሠረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች በተገቢው መንገድ ለመፈጸም የሚያስችል ፖለቲካዊ ተደማጭነትን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል፡፡ በተለይም ላለፈው አንድ ዓመት በክልሉ የተፈጠረው ግጭት እና የሰላም እጦት የክልሉን ገጽታ አጠልሽቶታል ያሉት አባላቱ የክልሉን ትክክለኛ ገጽታ በመገንባት እና ወንድማማችነትን በማስፈን በኩል ብዙ ርቀት መሄድ እንደሚጠይቅ አንስተዋል፡፡

በክልሉ በርካታ መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች ገብተው ይሠራሉ ያሉት የምክር ቤቱ አባላት አፈጻጸማቸውን በመከታተል እና ለውጡን በመገምገም በኩል ውስንነቶች እንዳሉ አንስተዋል፡፡ ይህንንም ክፍተት ለመሙላት የሚያስችል የማኅበራዊ ልማት ፈንድ ቢቋቋም የሚል ጥያቄ ሰንዝረዋል፡፡ በተጨማሪም የክልሉ መንግሥት የ2017 በጀት ዓመት የልማት እና የመልካም አሥተዳደር እቅድ ሀገሪቱ በቅርቡ ያሻሻለችውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ታሳቢ አድርጎ ቢከለስ የሚል ጥያቄዎችን ሰንዝረዋል፡፡

በሀገራዊ ምክክር ሂደት የክልሉ ዝግጁነት ምን ያክል እንደኾነ፣ የወሰን እና የማንነት ጥያቄዎችን ለመመለስ ምን እየተሠራ እንደኾነ፣ የሥራ እድል ፈጠራ እና መሰል ጥያቄዎችም በምክር ቤት አባላት ተጠይቀዋል።

ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱት ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ምላሽ እና ማብራሪያ የሰጡት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ለክልሉ መንግሥት የበጀት ዓመቱ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር እቅድ መሳካት የሰከነ ፖለቲካ፣ ቁርጠኛ መሪ፣ ቅንጅታዊ አሠራር እና የሕዝብ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

እቅዱን በተገቢው መንገድ ለመፈጸም የሚለኩ ተግባራትን ማስቀመጥ አንዱ የማስፈጸሚያ ስልት ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ እንደ ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን እና ቱሪዝም ዘርፎች የመንግሥትን ሚና ለይቶ ማስቀመጥ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ የልማት ሥራዎችን ከሥራ እድል ፈጠራ ጋር ማስተሳሰር እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

በግጭት የወደሙ አካባቢዎችን በልዩ ፈንድ ማገዝ እንደሚገባም ርእሰ መሥተዳድሩ አንስተዋል፡፡ በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ውስጥ የክልሉ ሕዝብ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ በንቃት ለመሳተፍ የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ነውም ብለዋል፡፡ የማንነት እና ወሰን ጥያቄዎች በዘለቄታዊ መንገድ እንዲፈቱ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየብሪክስ ወጣቶች ጉባዔ የአባል ሀገራቱ ወጣቶች በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ እንዲመክሩ እድል እንደፈጠረ ተገለጸ።
Next articleመድኃኒትነት ያላቸውን ችግኞች በመትከል የአረንጓዴ አሻራ ሥራን በውጤታማነት ለማከናወን እየሠራ መኾኑን ጤና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡