የብሪክስ ወጣቶች ጉባዔ የአባል ሀገራቱ ወጣቶች በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ እንዲመክሩ እድል እንደፈጠረ ተገለጸ።

15

ባሕር ዳር: ሐምሌ 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት የልዑክ ቡድን በቅርቡ በሩሲያ ኡልያኖስክ በተካሄደው 10ኛው የብሪክስ የወጣቶች ጉባዔ ተሳትፏል። ጉባዔው በአባል ሀገራቱ ወጣቶች መካከል ያለውን ትብብር እና አጋርነት ለማጠናከር በር የከፈተ እንደነበር የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ገልጿል።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ፋዓድ ገና በጉባዔው ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሁሉም የብሪክስ አባል ሀገራት የተወከሉ የወጣት መሪዎች እና ሚኒስትሮች መሳተፋቸውን ገልጿል። ኢትዮጵያም የብሪክስ ጥምረትን መቀላቀሏን ተከትሎ በጉባዔው ለመጀመሪያ ጊዜ መሳተፏን ተናግሯል።

ጉባዔው በትምህርት እና ሥልጠና፣ ሳይንስ፣ ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በጤና፣ በስፖርት እና በኪነ-ጥበብ ዙሪያ ላይ መምከሩን ጠቁሟል። ጉባዔው የአባል ሀገራቱን ወጣቶች በአንድ መድረክ በማሠባሠብ በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ እንዲመክሩ እና በመጻዒ ዕድላቸው እንዲወያዩ በር ከፍቷል ነው ያለው።

ጉባዔው በአጠቃላይ በብሪክስ አባል ሀገራት መካከል በወጣቶች ዘርፍ ያለውን ትብብር እና አጋርነት ለማጠናከር በር የከፈተ እንደነበር የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ወጣት ፉአድ ገና ገልጿል።

ከጉባኤው ጎን ለጎን የኢትዮጵያ ወጣቶችን ተሳታፊ እና ተጠቃሚ ማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ከቻይና፣ ከህንድ፣ ከብራዚል፣ ከኢራን እና ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የወጣት ሚኒስትሮች ጋር የሁለትዮሽ ውይይቶች መካሄዳቸውን ተናግሯል፡፡

የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ወጣቶች በተደራጀ አግባብ መብት እና ጥቅማቸውን እንዲያስጠብቁ እንዱሁም በሀገር ግንባታ ሂደት ላይ አዎንታዊ ሚና እንዲኖራቸው ተልእኮ አንግቦ የሚሠራ ተቋም ነው፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article390 ኢትዮጵያውያን ከሳዑዲ ዓረቢያ ወደ ሀገራቸው ተመለሱ።
Next articleየማንነት እና ወሰን ጥያቄዎች በዘለቄታዊ መንገድ እንዲፈቱ እየተሠራ መኾኑን ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ አስታወቁ፡፡