ተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎችን መከታተል እና መቆጣጠር እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡

12

ባሕር ዳር: ሐምሌ 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) እነዚህ በሽታዎች በዕድሜ መጨመር፣ በፈጣን የከተሞች መስፋፋት፣ ጤናማ ባልኾነ የአኗኗር ዘይቤ እና በሌሎች ምክንያቶች የሚከሰቱ ናቸው ይላሉ በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የሕክምና እና ታሃድሶ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ተወካይ አያናዉ ታከለ፡፡
እነዚህ በሽታዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰዎችን በከፍተኛ ሁኔታ ለሞት እየዳረጉ እንደኾነም ነዉ የገለጹት፡፡

በሀገራችን ብዙ አይነት ተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎች ይስተዋላሉ። ከእነዚህም መካከል የልብ እና የደም ቧንቧ በሽታዎች ወይም የልብ ድካም እና ስትሮክ፣ ካንሰር፣ ስር የሰደደ የመተንፈሻ አካላት በሽታዎች እና የስኳር በሽታ በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ለእነዚህ በሽታዎች መከሰት ምክንያት የሚኾኑት የደም ግፊት መጨመር፣ከፍ ያለ የደም ውስጥ ስኳር መጠን መኖር፣ አጠቃላይ የኮሊስትሮል ከፍ ማለት እና ከመጠን በላይ ውፍረት እንደኾኑ አቶ አያናው አብራርተዋል፡፡

ለአብዛኛዎቹ ተላላፊ ላልኾኑ በሽታዎች አጋላጭ መንስኤ የሚኾኑት ትምባሆ ማጨስ፣ ከፍተኛ የኾነ የአልኮል መጠጥ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ እና ጤናማ ያልኾነ የአመጋገብ ሥርአት እንደኾነ ነው የተናገሩት፡፡ እነዚህ በሽታዎች ሊሻሻሉ የማይችሉ ወይም የማይቀየሩ አጋላጭ ሁኔታዎች እና ሊሻሻሉ የሚችሉ ወይም ሊቀየሩ የሚችሉ አጋላጭ ሁኔታዎች ተብለዉ በሁለት እንደሚከፈሉም ያብራራሉ፡፡

ሊሻሻሉ የማይችሉ ወይም የማይቀየሩ አጋላጭ ሁኔታዎች የሚባሉት ዕድሜ፣ ጾታ እና ዘር ጋር ተያይዘዉ የሚመጡ ናቸው። እነዚህን በሽታዎች ማሻሻል እንደማይቻል ነገር ግን በአመጋገብ፣ በአካል እንቅስቃሴ እና በሕክምና ክትትል ባሉበት መቆጣጠር እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

ሊሻሻሉ የሚችሉ ወይም ልንከላከላቸዉ የሚችሉ አጋላጭ ሁኔታዎች የምንላቸዉን ደግሞ አካላዊ እንቅስቃሴ በማድረግ፣ ትማባሆ ባለማጨስ፣ በሚያጨሱ ሰዎች አካባቢ ባለመገኘት፣ አልኮል ባለመጠቀም እና ጤናማ ያልኾኑ የአመጋገብ ሁኔታዎችን በማስወገድ ልንቀንሳቸው እና ልንቆጣጠራቸዉ እንደምንችል ነው ያስረዱት፡፡

ተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎች በተለይ የሀገሪቱን አምራች ዜጋ በከፍተኛ ሁኔታ እያጠቁ እንደኾነ የሚናገሩት አቶ አያናው ይህም የሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያሳድር ተናግረዋል፡፡ አቶ አያናው ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በጤና ተቋማት በመደበኛነት አጠቃላይ ምርመራ በማድረግ የጤንነት ሁኔታቸውን መከታተል እና መቆጣጠር እንደሚገባው መክረዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየናይል ተፋሰስ ኮሚሽን መቋቋሙ የናይል ውኃ ሀብትን በጋራ ለማሥተዳደር እና ለማልማት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተገለጸ።
Next article390 ኢትዮጵያውያን ከሳዑዲ ዓረቢያ ወደ ሀገራቸው ተመለሱ።