
ባሕር ዳር: ሐምሌ 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የናይል ተፋሰስ ኮሚሽን በናይል ተፋሰስ ውኃ ሀብቶች የጋራ አጠቃቀም እና ልማት ላይ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው ተቋማዊ አሠራር ለመፍጠር እንደሚያስችል የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛንያ፣ ኡጋንዳ እና ብሩንዲ የናይል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን አስቀድመው በሀገራቸው የሕግ አውጪ ምክር ቤት ያጸደቁ ሀገራት ናቸው። ደቡብ ሱዳን ደግሞ ስምምነቱን ያጸደቀች ስድስተኛ ሀገር ስትኾን ይህም ስምምነቱን ወደ ሕጋዊ ተፈጻሚነት ምዕራፍ እንዲሸጋገር ያደርገዋል።
ማዕቀፉን ከፈረሙ 7 ሀገራት መካከል 2/3ኛው (ስድስት ሀገራት) ስምምነቱን በፓርላማ ሲያጸድቁ እና ያጸደቁበትን ሰነድ ለአፍሪካ ኅብረት ሲያስገቡ ኮሚሽኑን ማቋቋም ይችላሉ። የስምምነት ሰነዱ ላይ ኢትዮጵያን ወክለው ለረጅም ጊዜ ውይይት ያደረጉት የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ፤ በናይል ትብብር ማዕቀፍ ስምምነት አማካኝነት ኮሚሽኑ ሕጋዊ መሰረት ይዞ መቋቋሙ የናይል የውኃ ሀብትን በጋራ ማሥተዳደር እና ማልማት የሚያስችል ነው ብለዋል።
የኮሚሽኑ መቋቋም በውኃ ሀብቶች አሥተዳደር እና ጥበቃ ላይ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው ሕጋዊ እና ተቋማዊ አሠራር የሚፈጥር መኾኑንም ገልጸዋል። ኮሚሽኑ በተፋሰሱ ሀገራት መካከል ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ የውኃ አጠቃቀም እንዲኖር መሰረት እንደሚጥል ጠቅሰው ኢትዮጵያም የውኃ ሀብቷን በማዕቀፉ አማካኝነት በትብብር ለመጠቀም ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርላት ተናግረዋል።
በመኾኑም የስምምነት ሰነዱን ፈራሚ ሀገራት የፈረሙትን ሰነድ ለአፍሪካ ኅብረት በማስገባት ኮሚሽኑን በአጭር ጊዜ ማቋቋም እና ዓለም አቀፍ ዕውቅና እንዲያገኝ መሥራት አለባቸው ብለዋል። ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው ተቋማዊ አሠራር እንዲፈጠር አበክራ ሥትሠራ መቆየቷን ጠቅሰው በቀጣይም የኮሚሽኑ ሥራ ውጤታማ እንዲኾን የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ደቡብ ሱዳን ስምምነቱን እ.አ.አ ሐምሌ 8 ቀን 2024 በሀገሯ የሕግ አውጪ ምክር ቤት ካጸደቀችበት ጊዜ አንስቶ በሚቆጠር 60 ቀናት ውስጥ ማዕቀፉ ተፈጻሚ እንደሚኾን በሰነዱ ላይ ተመላክቷል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!