
ባሕር ዳር: ሐምሌ 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ጉባኤ ሁለተኛ ቀን ውሎ እንደቀጠለ ነው፡፡ በምክር ቤቱ መደበኛ ጉባኤ ሁለተኛ ቀን የረፋድ ቆይታ የክልሉ መንግሥት የ2017 በጀት ዓመት የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ዕቅድ ቀርቧል፡፡
የምክር ቤት አባላቱ የቀረበውን የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ዕቅድ ተከትሎ ጥያቄ እና አስተያየቶችን አንስተዋል፡፡ የምክር ቤት አባላቱ በተለይም ዕቅዱ በቅርቡ በሀገር ደረጃ ተግባራዊ የኾነውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ ታሳቢ ያደረገ እንዲኾን ትኩረት ሰጥተው ጥያቄዎቻቸውን እና አስተያየቶቻቸውን አንስተዋል፡፡
ክልሉ አሁን ባለበት የሰላም እጦት ላይ ኾኖ ዕቅዱን ለማሳካት ፈታኝ ሁኔታዎች ሊገጥሙት ይችላሉ ያሉት የምክር ቤት አባላቱ የክልሉን ሰላም ማረጋገጥ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ መኾን ይኖርበታል ብለዋል፡፡ በተለይም የክልሉ ምጣኔ ሃብት በዋናነት የተመሠረተበት የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ በተፈጠረው የሰላም እጦት ዕቅዱን ለማሳካት እንዳይቸገር ሰፋ አድርጎ ማየት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
የክልሉን መንግሥት የ2017 በጀት ዓመት የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ዕቅድ ለማሳካት የሚያስችል የተለየ ስልት ያስፈልጋል ያሉት የምክር ቤት አባላቱ ቅድሚያ መሰጠት የሚያስፈልጋቸውን ጉዳዮች ለይቶ ማስቀመጥም እንደሚያስፈልግ አንስተዋል፡፡ የምክር ቤት አባላቱ ዕቅዱ በቅርቡ በሀገር ደረጃ ተግባራዊ የኾነውን የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ትግበራ ከግምት ውስጥ ያስገባ መኾን እንደሚኖርበትም አንስተዋል፡፡
የማሻሻያ ትግበራው ይዞት የመጣውን መልካም ዕድል በሚፈለገው መጠን ለመጠቀም በትግበራ ወቅት የሚኖሩትን ፈተናዎች የሚያሻግር የተለየ ትኩረት ይጠይቃል ያሉት የምክር ቤት አባላቱ ዕቅዱ ከዚህ አንጻር መቃኘት ይኖርበታል ብለዋል፡፡ የዋጋ ንረትን፣ ዘመናዊ ግብርና እና ኢንዱስትሪ ትግበራ፣ ዘላቂ የልማት ፋይናንስ፣ የመሠረተ ልማት ግንባታ፣ የወጣቶች ብድር አቅርቦት እና ድህነት ቅነሳ በምክር ቤት አባላቱ በተለየ ትኩረት የተነሱ ቢኾንም የክልሉን ሰላም ማረጋገጥ እና ዘላቂ ሰላምን ማጽናት ግን የሞት ሽረት ጉዳይ ሊኾን እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡
ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥም አሁን የተጀመሩ ተስፋ ሰጪ የሰላም ሂደቶች ዳር እንዲደርሱ ሁሉም ኀይሎች በጋራ መሥራት አለባቸው ተብሏል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!